ክርስቲያን የቡና ግብይትና ሁለገብ የሕብረት ሥራ ማህበር በቡና ጥራት ዙሪያ በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን ገለፀ

ክርስቲያን የቡና ግብይትና ሁለገብ የሕብረት ሥራ ማህበር በቡና ጥራት ዙሪያ በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን ገለፀ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 03/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በኣሪ ዞን ክርስቲያን የቡና ግብይትና ሁለገብ የሕብረት ሥራ ማህበር የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችል በቡና ጥራት ዙሪያ በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን ገለፀ።

ማህበሩ በአሁን ወቅት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል እንዳለው የተገለፀ ሲሆን የ2017 አፈፃፀምና የ2018 በጀት አመት ዕቅድ ዙሪያ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በጂንካ ከተማ መክሯል።

በርካታ መሠረታዊ የሕብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒዬኖች የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሠሩ መሆናቸውን የገለፁት በአሪ ዞን የደቡብ አሪ ወረዳ ሕብረት ሥራ ልማት ፅሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሕዝቄል ናሽራይ እና በፅ/ቤቱ የኦዲት ባለሙያ አቶ አስጨርስ መኮንን፣ ክርስቲያን የቡና ግብይትና ሁለገብ የሕብረት ሥራ ማህበር በአጭር ጊዜ የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቁመው፥ ለማህበሩ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደረጉ አስረድተዋል።

ከ4ሺህ በላይ አባላት ያሉት ክርስቲያን የቡና ግብይትና ሁለገብ የሕብረት ሥራ ማህበር እስከ 15 ሚሊዮን ብር ካፒታል ማስመዝገባቸውን የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ሺቾ ጠቅሰው በአረንጓዴ አሻራ፣ በእንስሳት ግብይትና በለሎች ዘርፎችም እየሠሩ እንዳሉ አብራርተዋል ።

የማህበሩን የ2017 የአፈፃፀም ሪፖርት እና 2018 በጀት አመት ዕቅድን ለተሳታፍዎች ያቀረቡት አቶ ማቴዎስ አብርሃም በበኩላቸው የማህበሩን ውጤታማ ሥራዎችን በማስቀጠል ከ9 ሺህ ኩንታል በላይ ቡናን ለማዕከላዊ ገበያ ለመላክ አቅዶ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ማህበሩ የተሻለ ውጤት እንዳያስመዝግብ ማነቆ የሆኑ ጉዳዮች እንዲፈታላቸው የመድረኩ ተሳታፍዎች ጠይቀው ፤ በቀጣይ በጀት ዓመት የሕብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጠንክረው እንደሚሠሩም ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን