በላንክሻየር ደርቢ ሊቨርፑል ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል

በላንክሻየር ደርቢ ሊቨርፑል ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 27/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ20ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚዬርሊግ በሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ በላንክሻየር ደርቢ ሊቨርፑል ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም በሚካሄደው ጨዋታ በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል መሪነቱን ለማጠናከር እንዲሁም እጅግ የከፋ የውጤት ማጣት ውስጥ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ከገባበት የውጤት ቀውስ ለመውጣት የሚያደርጉት ፊልሚያ በመሆኑ የምሽቱ ጨዋታ ከወዲሁ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል።

የመርሲሳይዱ ክለብ በፈታኙ የቦክሲንግ ዴይ/የበዓል ሰሞን ያከናወናቸውን 3 ጨዋታዎችን ከማሸነፉ በተጨማሪ በተጋጣሚዎቹ ላይ 14 ግቦችን በማስቆጠር በ45 ነጥብ ሊጉን እየመራ ይገኛል።

በአንፃሩ ማንቸስተር ዩናይትድ በ3 ጨዋታዎች ሽንፈትን ያስተናገደ ሲሆን በእነዚህ ጨዋታዎች ምንም ጎል አላስቆጠሩም።

በደረጃ ሰንጠረዡም ከመሪው እና ታሪካዊ ባላንጣቸው ሊቨርፑል በ23 ነጥቦች ርቀው 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ይሁን እንጂ ወትሮውንም ቢሆን ሁለቱም ክለቦች በተመሳሳይ ጥሩ ብቃት ላይ ሳይሆኑ እንኳን በሚገናኙበት ወቅት እጅ ላለመስጠት የሚደረገው ትንቅንቅ በየዓመቱ በብዙሃኑ ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፎላቸዋል።

ሁለቱ ክለቦች በዛሬው ዕለት በሁሉም ውድድሮች ለ216ኛ ጊዜ እንዲሁም በሊጉ ለ184ኛ ጊዜ ይገናኛሉ።

በአንፊልድ 99ኛ ግጥሚያቸውን ነው የሚያካሂዱት።

25 ጊዜ ሊቨርፑልን ከሜዳው ውጪ ማሸነፍ የቻለው ማንቸስተር ዩናይትድ ባለፉት 8 ተከታታይ ጨዋታዎች በአንፊልድ ሊቨርፑልን ማሸነፍ አልቻለም። በ4 ተሸንፎ በ4ቱ አቻ ወጥቷል።

ሊቨርፑል በነዚህ 8 ጨዋታዎች አንድ ጎል ብቻ ነው በቀያይ ሰይጣኖች የተቆጠረበት።

ሞሀመድ ሳላህ ከየትኛውም ክለብ በላይ ማንቸስተር ዩናይትድ ላይ የጎል ተሳትፎ(18) አድርጓል።

የሊቨርፑል ክለብ የምንግዜም 4ኛው ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ማንቸስተር ዩናይትድ ላይ 12 ጎሎችን አስቆጥሮ 6 ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል።

በሊቨርፑል በኩል ኮነር ብራድሊ እና እብራሂማ ኮናቴ ከጉዳት ማገገማቸው ሲገለፅ ጆይ ጎሜዝ ግን ባጋጠመው ለምሽቱ ጨዋታ አይደርስም ተብሏል።

በማንቸስተር ዩናይትድ በኩል ቅጣት ላይ የነበሩት አምበሉ ብሩኖ ፈርናንዴዝ እና ማኑኤል ኡጋርቴ ወደ ጨዋታ የሚመለሱ ሲሆን ማርከስ ራሽፎርድ በህመም፣ ቪክቶር ሊንድሎፍ፣ ማሰን ማውንት፣ ሉክ ሾው እና ጆኒ ኢቫንስ በጉዳት ከወሳኙ ጨዋታ ውጪ መሆናቸው ተነግሯል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ