7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን በመንግስት በኩል ጠንካራ አቋም ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ በምክር ቤቱ 4ኛ ዙር 13ኛ አመት 30ኛ መደበኛ ጉባኤ በወልቂጤ ከተማ በተካሄደበት ወቅት ገልጸዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በመድረኩ ላይ እንዳሉት በዞኑ ባለፉት 6 ወራት የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን አመላክተዋል።
በገጠርና በከተማ ማህበረሰቡ ሲጠይቃቸው የነበሩ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሕዝብና የመንግስት አቅም በማስተባበር በተከናወነ ተግባር አመርቂ ውጤት እየተገኘ እንደሆነ ዋና አስተዳዳሪው አብራርተዋል ።
በዞኑ በተፋሰስ ልማት የጠረጴዛማ እርከን ባህል እየሆነ መጥቷል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፥ እንደአጠቃላይ በግብርው ዘርፍ እንደ ሃገር ሞዴል እና ተሞክሮ የተቀመረባቸው ተግባራት መከናወኑን ገልጸው፥ በዞኑ አንድም የማይታረስ መሬት መኖር የለበትም የሚል ግብ ተጥሎ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ባህር ዛፍ በዞኑ ለም መሬትና የውሃ አማራጮች እንዲባክኑ መንስኤ ከማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ በቅንጅት ወደ ተግባር ተገብቷል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፥ የኑሮ ውድነትን ለማርገብ የግብርና ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ተግባር እንደሆነም አስገንዝበዋል ።
ትምህርት ላይ የተማሪዎችን የአመለካከት ክፍተት በመሙላት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይነጠሉ ወላጆችን ጨምሮ የትምህርት ማህበረሰቡ ትምህርት ለዜጎችም ሆነ ለሀገር ብልጽግና የሚኖረው ጉልህ አስተዋጽኦ ለተማሪዎች በማስገንዘብ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት ማገዝ እንደሚገባ ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል።
በዞኑ ከተሞችን በማዘመን ለኑሮ ተስማሚ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው የኮሪደር ልማቱ ከማጠናከር ጎን ለጎን የተሰራውን ልማት ደህንነት መጠበቅ እንደሚገባም አስረድተዋል ።
የዞኑ አስተዳደር የጉራጌ የማህበረሰብ ቴሌቭዥን ጣቢያ ለመክፈት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፥ ለማስጀመሪያ ብቻ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ እንደሚጠይቅ በመጠቆም የባለሀብቱ እገዛና ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም ተናግረዋል።
በግማሽ በጀት አመቱ ከግማሽ ቢልየን ብር በላይ ገቢ ለመጀመሪያ ጊዜ ከእቅድ በላይ ተጨማሪ ገንዘብ መሰብሰቡን የጠቆሙት አቶ ላጫ ዞኑ ካለው አቅም እና የልማት ፍላጎት አኳያ በዘርፉ ገና ብዙ መስራት ይጠይቃል ብለዋል።
ከምክር ቤቱ አባላት የተነሱ ሃሳብ እና አስተያየቶች እንደ ግብዓት ተወስደው የቀጣይ ተግባር አካል ይደረጋሉ ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው።
የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ኸይሩ መሀመድ በበኩላቸው በዞኑ በፓርቲና መንግስት የሚሰጡ አቅጣጫዎችና ኢኒሼቲቮች ወደ ተግባር በመቀየር ባለፋት ስድስት ወራት በተከናወኑ ውጤታማ ስራዎች አበረታች ውጤት መመዝገቡን ማረጋገጥ እንደተቻለ ተናግረዋል ።
ዘንድሮ የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ እንዲሁም ተአማኒነት ያለው ምርጫ እንዲሆን በመንግስት ጠንካራ አቋም ተይዞ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ኸይሩ ምርጫ የዴሞክራሲ አንዱ መገለጫ መሆኑን በመገንዘብ የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን በመስራት ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
የቀረበው ሪፖርት መነሻ አድርገው የምክር ቤቱ አባላት በዞኑ ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው አበረታች ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እንዲሁም ክትትል በሚፈልጉ በተለይም በዞኑ የባህር ዛፍ በተገቢው ቦታ ብቻ መትከል፣ ወደ ዞኑ የሚገባው ነዳጅ በፍትሃዊነት ማሰራጨት፣ በተማሪ መፅሀፍት አቅርቦት፣ በንፁህ መጠጥ ውሃ፣ በትራንስፖርት አገልግሎት በመንገድና እና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ ሀሳብና አስተያየቶች አንስተዋል።
በተለይም የዘንድሮ 7ኛው ክልላዊና ሀገራዊ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ አሳታፊና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ቅንጅታዊ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እንደሚሰሩም የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።
የቀረበው ሪፖርት መነሻ አድርገው የምክር ቤቱ አባላት ላነሷቸው አስተያየቶች እና ጥያቄዎች የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እና የዞን መምሪያ የየዘርፍ ሀላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተውባቸዋል።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ የ2018 በጀት አመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት እንዲሁም የዞኑ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ የአቶ ነጋ አስፋው ሹመት በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
ዘጋቢ: ሪድዋን ሰፋ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
6ኛው የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ይገኛል
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የክልሉን ሕዝብ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ ገለጹ
ህዝቡ የሚያነሳቸውን የፍትህ ጥያቄዎች በአግባቡ ከመመለስ አኳያ የፍትህ ተቋማት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አሳሰቡ