የሐሞት ጠጠር በሐሞት ከረጢት ውስጥ በሚገኝ የሐሞት ፈሳሽ አልያም ሐሞትን ከጉበት ወደ አንጀት በሚወስዱ ቱቦዎች ውስጥ የሚፈጠር ባዕድ ነገር ነው።
የሐሞት ፈሳሽ በጉበት ሕዋሳት የሚመረት፣ ጨዋማ ንጥረ ነገሮችን ያዘለ ሲሆን የምንመገባቸው ቅባት እና ቫይታሚኖች እንዲፈጩ ይረዳል።
በሰውነታችን የሚገኙ መርዛማ ንጥረ ነገሮችን ለማጥፋት ጠቃሚ እንደሆነም በደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ከሆሳዕና ቅርንጫፍ ጋር ቆይታ ያደረጉት በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የንግስት እሌኒ መሐመድ መታሰቢያ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት ዶክተር አዳነ ደስታ ናቸዉ::
80 በመቶ የሚሆነው የሐሞት ጠጠር የሚከሰተው በቅባት አልያም በኮሌስትሮል መብዛት መሆኑንም ዶክተር አዳነ ይናገራሉ።
የሐሞት ጠጠር ተጋላጭነትን ከሚጨምሩ ነገሮች መካከል ቅባታማ ምግቦችን ማዘውተር፣ ከልክ ያለፈ ውፍረት፣ በእርግዝና ወቅት ከልክ ያለፈ ውፍረትና የዕድሜ መግፋት የሚጠቀሱ መሆናቸውን የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስቱ አስገንዝበዋል::
የሐሞት ጠጠር ለረዥም ጊዜ የህመም ስሜት ሳይሰማ ሊቆይ ይችላል ያሉት ዶክተር አዳነ ሐሞት የሚወጣበት ቱቦ በጠጠር በሚዘጋበት ጊዜ በቀኝ በኩል የሆዳችን የላይኛው ክፍል ላይ ሄድ መለስ የሚል ወይም የማያቋርጥ የሕመም ስሜትን ያስከትላል ሲሉም አክለዋል።
ቅባት ነክ ምግቦችን ስንመገብ ያለመስማማት፣ ከምግብ በኋላ የሚፈጠር የመጠዝጠዝ ስሜት፣ የማቅለሽለሽ እና የማስመለስ ችግር፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ በሰውነት ላይ ቀያይ ነጠብጣብ መታየት፣ የሰገራ ቀለም መቀየር የሐሞት ጠጠር ምልክቶች መሆናቸውንም ነግረውናል።
የሐሞት ጠጠርን ለመከለከል የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ የምግብ ሰዓትን አለማሳለፍና በቂ ውኃ መጠጣት እንደሚገባም ጠቁመዋል::
ከፍተኛ ከሆነ የቅባት ምግቦችን አለመመገብ እና የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶችን መውሰድ የሕመም ስሜትን ለጊዜው ያስታግሳል ያሉት ዶክተር አዳነ ሕመሙ እየበረታ ከሄደ ግን የሐሞት ጠጠሩን በቀዶ ሕክምና ማውጣት እንደሚገባ ይመክራሉ።
ዘጋቢ: በየነ ሰላሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በሥራ ዕድል ፈጠራ የተደራጁ ወጣቶች ከተጠቃሚነታቸው ባለፈ በፈጠራ ስራቸው ለማህበረሰቡ ችግር ፈቺ አገልግሎቶችን እየሰጡ እንደሆነ ተገለጸ
በክልሉ ከሚገኙ ሁሉም ተቋማት ጋር የመረጃ ግንኙነት በማጠናከር በሁሉም ዘርፎች የህብረተሰቡን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው – የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ
የገና ሰሞን በጉራጌ !!!