‎ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ  እስኪጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር እና የወረዳዋ ነዋሪዎች ተናገሩ

ግድቡን ለማጠናቀቅ የሚያስችል ገቢ የማሰባሰብ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳና ከተማ አስተዳደሮች አስታውቀዋል፡፡

‎ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማጠናቀቅ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን የገባው የህዳሴ ግድብ ዋንጫ በዞኑ ገደብና ኮቾሬ ወረዳ የነበረውን ቆይታ በማጠናቀቅ ይርጋጨፌ ከተማ ደርሷል፡፡

‎ዋንጫውን የተረከቡት የይርጋጨፌ ከተማና ወረዳ አስተዳደሮችም ሁሉን የህብረተሰብ ክፍሎችን ባሳተፈ መልኩ በአጠቃላይ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የመሰብሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

‎በዞኑ የይርጋጨፌ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ክፍሌ ጅግሦ እንዲሁም የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ታደለ ጥላሁን የይቻላል መንፈስ ማረጋገጫ የሆነውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማጠናቀቅ ወረዳና ከተማ አስተዳደሮች በጋራ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ በማቀድ ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውቀዋል፡፡

‎የህዳሴ ግድብ ግንባታው ካለው ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጠቀሜታ በተጨማሪ የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል ከማዳበር አኳያ ያለውን ፋይዳ በመረዳት ሁሉም ቦንድ በመግዛት ገቢ በማሰባሰብ ሥራ የተለመደውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

‎በዋንጫ አቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ወቅት በርካቶች ቦንድ በመግዛት ለግድቡ መጠናቀቅ ላሳዩት ድጋፍ ኃላፊዎቹ አመስግነዋል፡፡

‎አስተያየታቸውን ለደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሰጡ የይርጋጨፌ ከተማና ወረዳ ነዋሪዎች ታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያንን ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚያወጣና የህዝቡን አንድነትና ትብብር ለዓለም ያሳየ የዚህ ዘመን ትውልድ የታርክ አሻራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‎የህዳሴ ግድብ ሥራው ወደ መጠናቀቁ በመቃረቡ መደሰታቸውን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ ቀሪ ሥራዎችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተደረገ ያለውን ርብርብ በመደገፍ ቦንድ በመግዛት የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

‎ዘጋቢ ፡ ሳሙኤል በቀለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን