የማሌ ብሄረሰብ ዘመን መለወጫ “ዶኦሞ በዓል ለሠላምና ለአንድነት ” በሚል መሪ ቃል ተከበረ

ሀዋሳ: ታህሳስ 25/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማሌ ብሄረሰብ ዘመን መለወጫ “ዶኦሞ በዓል ለሠላምና ለአንድነት ” በሚል መሪ ቃል በጂንካ ማረሚያ ተቋም የሚገኙ የህግ ታራሚዎችና በጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል የሚገኙ ታካሚዎችን በመጠየቅ ነው የተከበረው።

ለማሌ ብሄረሰብ ዘመን መለወጫ “ዶኦሞ” በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ኦሞ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ሁሉአገርሽ አልቴ ናቸው።

በመረሃ ግብሩ ላይ የብሄረሰቡ ዘመን መለወጫ ዶኦሞ ዕሴቶች አንዱ የሆነውን የመጠያየቅ ዕሴት ለማጎልበትና በወረሃ ጥር 1 ለሚከበረው ዘመን መለወጫ ባሉበት ቦታ ሆነው መልካም ዕሴቱን በጠበቀ መልኩ ማክበር እንዲችሉና ሰላምን ለማስቀጠል ታስቦ መዘጋጀቱን ጠቁዋል።

ዶኦሞ በዓል የመጠያየቅ፣ የመተጋገዝና የመረዳዳት እሴት በመሆኑ ለትውልድ በቀጣይነት ለማስተላለፍ የሁሉም ህብረተሰብ ክፍል ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ያሉት የማሌ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ የመንግስት ረ/ተጠሪና የፓርቲው ፖለቲካና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙሃባ ሙሄ ናቸዉ።

የጂንካ ማረሚያ ፖሊስ ተቋም አዛዥ ም/ኮማንደር አስቻለው ኔሬሬ በበኩላቸው የማሌ ብሄረሰብ ደኦሞ በዓል እሴት የሆነውን መጠያየቅና መተዛዘን እንዲሁም መተጋገዝን ተማሪዎች በተግባር ስላሳዩ አመስግነዋል፡፡

በተመሣሣይ የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስክያጅ ዶ/ር ምስጥሩ ሐምዳኪ የዶኦሞ እሴት የሆነውን እረስ በርስ የመጠያየቅና የመደጋገፍ እሴት ያለበትን ዶኦሞ በዓል ምክንያት በማድረግ በሆስፒታሉ ተኝቶ የሚታከሙና በማቆያ የሚገኙ እናቶች በመጎበኘት አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ ለሳዩት መልካምነት አመስግነው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።

የበዓሉ ዋዜማ ተሳታፊ ከሆኑት አቶ ዘማ ጎርቃ ፣ ሙስጠፋ ሱልጣንና ሌሎችም በዓሉ ላለፉት ጊዜያት በተለያዩ አከባቢዎች ሲያከብሩ እንደነበሩ ገልጸው በዓሉን ምክንያት በማድረግ በሁለቱ ተቋማት የሚገኙ ግለሰቦችን በመጠየቅ ማክበራቸውን ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ ማማዬ ዲማኮ – ከጂንካ ጣቢያችን