በመኸር እርሻ ከሚለሙ ስብሎች ጥሩ ምርት ለማግኘት ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ እንደሚገኙ በዳውሮ ዞን ሎማ ቦሣ ወረዳ የሚገኙ አርሶአደሮች ተናገሩ

በመኸር እርሻ ከሚለሙ ስብሎች ጥሩ ምርት ለማግኘት ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ እንደሚገኙ በዳውሮ ዞን ሎማ ቦሣ ወረዳ የሚገኙ አርሶአደሮች ተናገሩ

‎የወረዳው ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ኀብረት ሥራ ልማት ጽህፈት ቤት በበኩሉ ከ11 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በዘር መሸፈኑን አስታውቋል።

‎በወረዳው ዋና ዋና ሰብሎች የሚባሉት ጤፍ፣ አተር፣ ባቄላ፣ ኦቾሎኒ፣ ገብስ፣ ስንዴና የመሳሰሉት ሰብሎች መሆናቸው ተመላክቷል።

‎ታዲያ እነዚህን ሰብሎች አምርቶ የሚፈልገውን ምርት ለማግኘት አርሶአደሮቹ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ እንደሚገኙ በወረዳው ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው አርሶአደሮች ይናገራሉ።

‎መሬታቸውን ደጋግመው በማረስ፣ ምርጥ ዘርን ጨምሮ ሙሉ ፓኬጅ ግብዓት በመጠቀም ማሳቸውን በዘር እየሸፈኑ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

‎እንዲሁም ሰብሉ በአረም እንዳይዋጥ ከወዲሁ ሳንዘናጋ የአረም ቁጥጥር ስራ እየተገበርን እንገኛለን ብለዋል።

‎የግብርና ባለሙያዎች፣ ሙያዊ እገዛ፣ ክትትልና ቁጥጥር ማድረጋቸው ለሥራችን ይበልጥ ትኩረት እንድንሰጥ አድርጎናል ብለዋል።

‎በወረዳው ከሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች መካከል አቶ ታምራት ታደሰ እና አቶ ባትሣ ሌሱ በሰጡት አስተያየት አርሶአደሮቹ ከመኸር እርሻ የተፈለገውን ምርት እንዲያገኙ ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ግብዓት አጠቃቀም ድረስ ሁልጊዜ በአርሶአደሩ ማሳ በመገኘት ሙያዊ እገዛ እንዲሁም ክትትልና ቁጥጥር እናደርጋለን ብለዋል።

‎የአየር ጠባይ ሁኔታም እስካሁኑ ድርስ ምቹ መሆኑን የተናገሩት ሙያተኞቹ ከመሬት ብቅ ያሉት እንደ ባቄላና የመሳሰሉትን ሰብሎች የአረም ቁጥጥር ስራ በተገቢው እየተተገበረ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

‎የወረዳው ግብርና፣ አካባቢ፣ ጥበቃና ኅብረት ሥራ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኪዳኔ በቀለ በበኩላቸው፤ በወረዳው ባሉት ሁሉም ቀበሌያት በመኸር እርሻ ወቅት 11 ሺህ 15 ሄክታር ማሳ በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዉ ይህ ዜና እሰከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 10 ሺህ 797 ሄክታር ማሳ በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።

‎በአጠቃላይ ከሚለማው ማሳ 2 መቶ 35 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱንም አስታውቀዋል።

‎የታቀደውን ምርት ለማግኘት 2 ሺህ 800 ኩንታል ዩሪያና 1 ሺህ 800 ኩንታል ዳፕ መጠቀማቸውን እንዲሁም የአረም ቁጥጥር ፀረ ተባይ ኬሚካል እርጭት ለማድረግ እንደተዘጋጁም ገልጸዋል።

‎በተጨማሪም በወረዳው የሚገኙትን የግብርና ሙያተኞችን ጨምሮ ሌሎችም አመራሮች ወደ አርሶአደሩ ማሳ በማውረድ ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርጉም ኃላፊው አክለዋል።

‎ዘጋቢ፡ አሸናፊ ግዛው – ከዋካ ጣቢያችን