ከ800 ሺህ ሊትር በላይ ዘይት ማሰራጨቱን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ

ከ800 ሺህ ሊትር በላይ ዘይት ማሰራጨቱን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 23/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከ800 ሺህ ሊትር በላይ የፓልም ዘይት በክልሉ ለሚገኙት ዞኖች ማሰራጨቱን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትልና የንግድ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አምዴ ፋሪስ እንደገለፁት በሚቀጠሉት ሳምንታት እንደ ክልልም ሆነ እንደሀገር ከሚከበሩ ሁለት ሐይማኖታዊ በዓላት መካከል የልደትና ጥምቀት በዓላት መኖራቸውን ጠቁመው፥ በበዓላት ወቅት ህዝቡ አዘውትሮ ከሚጠቀምባቸው ምርቶች መካከል የምግብ ዘይት አንዱ በመሆኑ በክልሉ ለሚገኙት 6ቱ ዞኖች በሁለት ዙር 858 ሺህ 400 ሊትር ዘይት በሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት በኩል እንዲሰራጭ መደረጉን ተናገረዋል።

ከፍጆታ ምርቶች ጋር ተያይዞ በምግብ ዘይት ላይ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን የገለፁት አቶ አምዴ፥ በድጎማ የሚቀርቡ ምርቶችን ከገበያ የማስገባትና ገበያውን የማረጋጋት ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም ከስኳር ጋር ተያይዞ በሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት በኩል ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን እንዲቀርብ እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው አውስተዋል።

በነፃ ገበያ ስርዓት የሚቀርብ የምግብ ዘይትና ስኳር ምርቶች አቅርቦቱን ለማሻሻል ከጅምላ አቅራቢዎች ጋር ውይይት እንዲደረግ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ አምዴ አሰረድተዋል።

በመንግስት ድጎማ የሚቀርቡ የምግብ ዘይት ምርቶች ለተጠቃሚው ህብረተሰብ በተገቢውና በፍትሃዊነት እንዲደርስ በማድረግ በኩል በየደረጃ የሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ኃላፊው አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን