የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የትምህርት ቤቶች አካል ብቃት እንቅስቃሴ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ተካሄደ
በትምህርት ቤቶች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማስጀመሪያ መርሃ-ግብር የተጀመረው በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ አስተዳደር በሶሬ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡
በማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አህመዲን አወል፤ በትምህርት ቤቶች የተጀመረው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን በመረዳት ተግባራትን ከትምህርት ቤቶች ለመጀመር በተያዘው እቅድ መነሻነት የተጀመረ መሆኑን አመላክተዋል።
እንደ ክልል በትምህርት ማህበረሰቡ ዘንድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ግንዛቤ በመፍጠር ጤናው የተጠበቀ ዜጋን የማፍራት አላማው ያደረገ ነው።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ቦታ ሳይመረጥ በሁሉም ቦታ መሠራት ያለበት ነው። እንቅስቃሴ ማድረግ ራስን ከተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ለመከላከል እንዲሁም የተሟላ ተክለ ሰውነት እንዲኖር የሚያደርግ በመሆኑ ሁሌም መሥራት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የዳውሮ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ደምሴ፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማከናወን በትምህርት ብቁ ዜጋ የሚያደርግ በመሆኑ ስፖርትን ሁሌም መስራት አለባችሁ ሲሉ ተናግረዋል።
ከትምህርት ቤቱ ተማሪዎች መካከል ተማሪ መድሃኒት ፈለቀ፣ ታፊሎስ ሳሙኤል፣ መሪሲል አለሙ በጋራ በሰጡን አስተያየት፤ በትምህርት ቤታቸው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በየዕለቱ የሚከወን መሆኑን የገለጹ ሲሆን ይኸውም በትምህርት ውሏቸው ንቁ ሆነው ወደ ትምህርት ገበታ እንዲገቡ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል።
የሶሬ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስፖርት መምህር ማንዴላ ጌታቸው እንደገለጹት፤ ትምህርት ቤቶች የስፖርተኛ መፍለቂያ ናቸው።
በመሆኑም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በትምህርት ቤቶች የተጀመረው መርሃ ግብር መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑን ገልጸው ማንኛውም ዜጋ ስፖርትን የሰርክ ተግባሩ ቢያደርግ ለጤንነት፣ ለማህበራዊ ህይወት እንዲሁም በተግባሩ ንቁ እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ አዲስዓለም ታዬ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የጅቡቲ አቻውን 6ለ1 አሸነፈ
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ የምስክር ወረቀት ተሰጠው
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ከአፍሪካ 1ኛ ከዓለም 3ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች