በቦክሲንግ ዴይ 8 የጨዋታ መርሐግብሮች ዛሬ ይካሄዳሉ

በቦክሲንግ ዴይ 8 የጨዋታ መርሐግብሮች ዛሬ ይካሄዳሉ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 17/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በእንግሊዝ ፕሪሚዬርሊግ የገና በዓል ማግስት (ቦክሲንግ ዴይ) 8 ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ይካሄዳል።

የእንግሊዝ ፕሪሚዬርሊግን ከሌሎች ሀገራት ሊጎች ለየት በሚያደርገው በዚህ የበዓል ሰሞን ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ላይ በኤቲሀድ ስታዲየም ማንቸስተር ሲቲ ከኤቨርተን ጋር ይጫወታሉ።

በተጫዋቾች መጎዳት እና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ውጤታማ ከመሆን አንፃር አስቸጋሪ ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ በሊጉ ከ3 ጨዋታዎች ያለማሸነፍ ጉዞ በኋላ ከድል ጋር ለመገናኘት ይጫወታል።

ከወራጅ ቀጠናው በ4 ነጥቦች ብቻ ርቆ 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባለፉት 2 ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለቱን የለንደን ከተማ ክለቦች አርሰናልን እና ቼልሲን ነጥብ ማስጣሉ አይዘነጋም።

ቢሆንም ግን በአሰልጣኝ ሰንዳይች የሚመራው የመርሲሳይዱ ክለብ በመከላከሉ ያለውን ጥንካሬ ወደ ማጥቃቱ ማሻገር አለመቻሉ እንደ ክፍተት ይነሳበታል።

ካለፉት 7 ጨዋታዎች በ6ቱ ጎል ሳያስቆጥር ከሜዳ የወጣው ኤቨርተን በፕሪሚዬርሊጉ እስካሁን 11 ጎሎችን ብቻ ካስቆጠረው ሳውዝሃምተን በመቀጠል አነስተኛ(14) ጎል ያስመዘገበ ክለብ ሆኖ ተቀምጧል።

ማንቸስተር ሲቲ ከኤቨርተን ጋር ባከናወናቸው የመጨረሻ 14 ጨዋታዎች ሽንፈትን አልቀመሰም። ለመጨረሻ ጊዜ በኤቨርተን እንደ አውሮፓውያኑ በ2017 4ለ0 በሆነ ውጤት የተሸነፉት ውሃ ሰማያዊ ለባሾች በሜዳቸውም በቅርቡ በአሜሪካውያን ባለሀብቶች ስር በገባው ክለብ ባለፉት 13 ግንኙነቶች አልተረቱም።

አመሻሽ 12 ሰዓት ላይ 5 ጨዋታዎች የሚከናወኑ ሲሆን በስታንፎርድ ብሪጅ በለንደን ደርቢ ሁለቱ የምዕራብ ለንደን ከተማ ክለቦች ቼልሲ እና ፉልሃም የሚያከናውኑት ጨዋታ ይጠበቃል።

ሁለቱም ክለቦች በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ቢገኙም ከአቻ ውጤት ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይፋለማሉ።

በአሰልጣኝ ኤንዞ ማሬስካ የሚመራው ቼልሲ በሁሉም ውድድሮች ከ8 ተከታታይ ማሸነፍ ቀኋላ እንዲሁም በሊጉ ከ5 ተከታታይ ድል በኋላ ባለፈው ዕሁድ ከኤቨርተን ጋር በአቻ ውጤት መለያየቱ ይታወሳል።

በፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ማርኮ ሲልቫ የሚሰለጥነው ፉልሃም የመጨረሻዎቹን 5 ጨዋታዎች ባይሸነፍም ባለፈው ሳምንት ከሳውዝሃምተን ጋር ያከናወነውን ጨዋታ እንደዛሬው ተጋጣሚ ያለጎል በአቻ ውጤት ነው ያጠናቀቀው።

በተደጋጋሚ የቼልሲ የበላይነት በሚታይበት የሁለቱ ግንኙነት ፉልሃም ሰማያዊዎቹን ካለፉት 34 ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ ነው መርታት የቻለው።

ቼልሲ በሜዳው በፉልሃም ለመጨረሻ ጊዜ የተረታው እንደ አውሮፓውያኑ በ1979 2ለዐ በሆነ ውጤት ነው።

በተመሳሳይ ሰዓት ኒውካስል ከአስቶንቪላ፣ኖቲንግሃም ፎረስት ከቶትንሃም እንዲሁም ሳውዝሃምተን ከዌስትሃም ይጫወታሉ።

ምሽት 2 ሰዓት ከ3ዐ ላይ በሁለቱ ፖርቹጋላዊያን አሰልጣኞች የሚመሩት ዎልቭስ እና ማንቸስተር ዩናይትድ በሞሊኑክስ ስታዲየም ይገናኛሉ።

ከጋሪ ኤኔል ስንብት በኋላ የ56 ዓመቱን ፖርቹጋላዊ አሰልጣኝ ቪቶር ፔሬራን የቀጠሩት ዎልቭሶች ከአራት ተከታታይ ሽንፈት ተላቀው ሌስተርን ከሜዳቸው ውጪ 3ለ0 በሆነ ውጤት መርታታቸው ይታወቃል።

ስራቸውን በድል የጀመሩት ቪቶር ፔሬራ በሜዳቸው እና በደጋፊያቸው ፊት የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በወር ልዩነት ከሳቸው ቀደም ብለው ወደ እንግሊዝ ከመጡት ከሀገራቸው አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ጋር ያከናውናሉ።

እንዲሁም ምሽት 5 ሰዓት ላይ ደግሞ በታሪኩ ለ21ኛ ጊዜ የሊጉ መሪ ሆኖ ገናን የተቀበለው ሊቨርፑል በሜዳው ሌስተርን ያስተናግዳል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ