አስቶንቪላ ከማንቸስተር ሲቲ እንዲሁም ክርስቲያል ፓላስ ከአርሰናል ዛሬ ይጫወታሉ

የእንግሊዝ ፕሪሚዬርሊግ  17ኛ ሳምንት በዛሬው ጅማሮውን ሲያደርግ አስቶንቪላ ከማንቸስተር ሲቲ እንዲሁም በለንደን ደርቢ ክርስቲያል ፓላስ ከአርሰናል ይጫወታሉ።

ቀን 9 ሰዓት ከ30 ላይ በቪላ ፓርክ አስቶንቪላ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር የሚያከናውኑት ጨዋታ ይጠበቃል።

ላለፉት 45 ቀናት ያኽል ከፍተኛ የሆነ የውጤት ችግር ውስጥ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ ከችግሩ ለማገገም ይጫወታል ተብሎ ይታሰባል።

በአሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ የሚመራው የማንቸስተር ከተማው በሁሉም ውድድሮች ካለፉት 11 ጨዋታዎች በ8ቱ ሽንፈትን አስተናግዷል።

በአስቶንቪላ በኩል በቀኑ ጨዋታ ከጃኮብ ራምሴ በስተቀር ሌሎች ተጫዋቾች ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው ተብሏል።

በማንቸስተር ሲቲ በኩል ሪኮ ከቅጣት እንዲሁም ማኑኤል አካንጂ እና ጆን ስቶንስ ከጉዳት በማገገም ለጨዋታው እንደሚደርሱ ሲገለፅ ናታን አኬ እና ሩበን ዲያዝ ግን በጉዳት አይሰለፉም ተብሏል።

ምሽት 2፡ሰዓት ከ30 ላይ በለንደን ደርቢ ክርስቲያል ፓላስ ጋር በሴልሃርስት ፓርክ ስታዲየም ይፋለማሉ።

የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ከሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

በክርስቲያል ፓላስ በኩል ኤቤሬቼ ኤዜ እና ወጣቱ አማካይ አዳም ዋርቶን በጉዳት ምክንያት ለጨዋታው አይደርሱም ተብሏል።

በአርሰናል በኩል ዴክላን ራይስ፣ሪካርዶ ካላፊዮሪ፣ኦሌክሳንደር ዚንቼንኮ ካጋጠማቸው ጉዳት በማገገም ወደ ደቡብ ለንደን ባቀናው ስብስብ መካተታቸው ተገልጿል።

በፕሪሚዬርሊጉ ሌሎች የዛሬ መርሐግብሮች በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ብሬንትፎርድ ከኖቲንግሃም ፎረስት፣ኢፕሲች ታውን ከኒውካስል ዩናይትድ እንዲሁም ዌስትሃም ዩናይትድ ከብራይተን ይጫወታሉ።

በሙሉቀን ባሳ