ስፖርት ለጤና ከሚሰጠው ጥቅም በዘለለ ሕዝቡን በማቀራረብ ወንድማማችነትን ለመፍጠር የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ታህሳስ 07/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ስፖርት ከሚሰጠው የጤና ጥቅም በዘለለ ሕዝቡን በማቀራረብ ወንድማማችነትን ለመፍጠር የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው የጎፋ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ፡፡
በሳውላ ከተማ ከጥቅምት 24 ጀምሮ በስምንት የጤና ቡድኖች መካከል ሲካሄድ የነበረው የእግር ኳስ ውድድር ተጠናቋል።
የጎፋ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ምክትልና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጠንክር ግዛቸው፥ ፈታ ካፕ በዞኑ ባዘጋጀው የስፖርት ውድድር የከተማው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ መነቃቃቱን ገልጸው፥ ንቁ፣ ጤናማ እና አምራች ዜጋን ለመፍጠር በስፖርት የዳበረ ማህበረሰብ መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሕብረተሰቡ በግልም ሆነ በቡድን በጤና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ከመከላከል ባሻገር ወንድማማችነትን የሚያጎለብት በመሆኑ የሁልጊዜ ተግባር ሊያደርጉት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሳውላ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መካከል በተደረገው የፍጻሜ ጨዋታ የሳውላ ፖሊ ቴክኒክ ኮለጅ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት ተጋጣሚውን በማሸነፍ በክልሉ ለሚደረገው ውድድር ማለፉን አረጋግጧል።
ለደረጃ በተደረገው ውድድር ፍቅር መናኻሪያ እና ሳውላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመደበኛ ሰዓት ሁለት አቻ በመለያየታቸው አሸናፊውን ለመለየት በተሰጠው የመለያ ምት ፍቅር መናሄሪያ 5 ለ 3 በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን አግኝቷል።
የፈታ ቢራ ተወካይ አቶ ቻንድራ አወል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ ወላይታ ሶዶ፣ አርባምንጭ፣ ጂንካ እና ሳውላ ከተሞች በ42 የጤና ስፖርት ቡድኖች መካከል ሲካሄድ የነበረው ውድድር ከ 15 ቀናት በኋላ የአራቱ ከተሞች አሸናፊ ክለቦች በክልል ደረጃ የፍጻሜ ውድድር እንደሚያካህዱ ገልጸዋል።
የጤና ቡድን አባላቱ ለአከባቢያቸው ብሎም ለከተማዋ የስፖርት እድገት ከፈታ ጋር በጋራ ለመስራት ያሳዩትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
ለውድድሩ መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትና ለተሳታፊ ክለቦች የዕውቅና ምስክር ወረቀት በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ እና በሳውላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እርቦላ እርኮ ተበርክቶላቸዋል።
ዋና አስተዳዳሪው በመልዕክታቸው የጤና ስፖርት ከሚሰጠው የጤና ጥቅም በዘለለ ሕዝቡን በማቀራረብ ወንድማማችነትን ለመፍጠር ጠቀሜታ እንዳለው አስገንዝበዋል።
የስፖርቱ ማህበረሰብ የዞኑ አምባሳደር የሆነውን ባራንቼ የስፖርት ክለብን ለማጠናከር የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ: አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
የሊጉ መሪ ሊቨርፑል ከቶትንሃም ጋር ዛሬ የሚያከናውኑት ጨዋታ ይጠበቃል
ማንቸስተር ሲቲ በአስቶንቪላ ተሸነፈ
አስቶንቪላ ከማንቸስተር ሲቲ እንዲሁም ክርስቲያል ፓላስ ከአርሰናል ዛሬ ይጫወታሉ