ሀዋሳ፡ ታህሳስ 01/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል በሚሰሩ ተግባራት ዙሪያ ምክር ቤቶችና የሚመለከታቸው አስፈፃሚ አካላት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የሸኮ ወረዳ ዋና አስተዳደር አስታወቀ።
የወረዳው ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ የአስተዳደር ም/ቤት የ1ኛ ሩብ ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት በመገመገም ተጠናቋል።
በምክር ቤቱ ሪፖርት የመጡ ለውጦችን በማጠናከር በዕጥረቶች ላይ ትኩረት ሰጥተው በመሥራት በሁሉም ዘርፍ የህዝብ ተጠቃሚነትን ማሳለጥ እንደሚገባ ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ጌታቸው ኮምቱ ገልፀው በ2ኛ ሩብ ዓመት ለተሻለ አፈጻጸም ጥረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል።
ምክር ቤቱ የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሚያደርገው ክትትልና ቁጥጥር ስራ በተጨማሪ መደበኛ ጉባኤ በማድረግ ተግባራትን መገመግም እንዳለበት ምክትል አፈ ጉባኤው ገልፀዋል።
የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አሰፋ ሸዋ በበኩላቸው በወረዳው በሚከናወኑት ተግባራት የተደረገ የሚገኘው ተሳትፎ አበረታች መሆኑን ጠቅሰው፥ አባላቱ በአካቢያቸው በሁሉም ዘርፎች ግምባር ቀደም የልማት ተዋናይ በመሆን የተጣለባቸውን ህዝባዊ ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሪ ጉርሙ የአስተዳደር ም/ቤት የ1ኛ ሩብ ዓመት አፈፃፀም ሪፖርትን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት በወረዳው የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ኑሮ በማሻሻል ረገድ ምክር ቤቶችና የሚመለከታቸው አስፈፃሚ አካላት ተቀናጅተው በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናገረዋል።
አርሶ አደሩ በግብርና ምርት ላይ ትኩረት በመስጠት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ እንዲላቀቁ ምክር ቤቶችና በየደረጃ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በተገቢው ሊወጡ እንደሚገባም ዋና አስተዳደሪው ገልፀዋል።
በዚህም በ1ኛ ሩብ አመት በተለያዩ አዝርዕት ከ2 ሺህ118 ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን አቶ አሪ ተናገረዋል።
የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጋን በመፍጠር ረገድ ትምህርት የሚያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛው እንደሆነና 11 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙ ሲሆን ትምህርት ቤቶችን ምቹ በማድረግ በኩል በተሰሩ ስራዎች ከ115 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው የመማሪያ ቁሳቁሶች እድሳት መደረጉን ዋና አስተዳደሪው አብራርተዋል።
በጤናው ዘርፍ የተዘነጋውና የወረረሽኝ መጠኑን እየጨመረ ያለውን ኤች አይ ቪ ኤድስን በመከላከል ረገድ የሁሉም ጉዳይ እንደሆነ አቶ አሪ አውስተው፥ በወባ ወረርሽኝ መከላከል ስራ 10 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ የማፋሰስ ስራ ቢከናወንም የህብረተሰብ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
በወረዳው የህግ የበላይነትን በማስከበርና በደን ላይ እየደረሰ የለውን ጉዳት በመከላከል ረገድ ከፖሊስ ፍትህ እና ፍርድ ቤቶች ጋር ቅንጅታዊ ሥራን በማጠናከር የህዝብና የመንግስት ጉዳዩች ላይ ዕልባት ሊሰጥ እንደሚገባ ከምክር ቤት የጉባኤ አባላት ጥያቄና አስተያየት ቀርቧል።
በህብረተሰብ ተሳትፎና በ350 ሚሊዬን ብር እየተገነባ ያለው የዳማ ወንዝ ድልድይ ያለበት ደረጃ፣ የደንና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ የኡሲቃ ፍልውሃና የመንገድ ልማት ሥራ፣ በመንገድ ደህንነት የትራንስፖርት ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ በህብረት ሥራ በጫኝና አውራጅ ማህበር ላይ የተስተዋሉ ችግሮች እንዲፈቱ የምክር ቤት የጉባኤ አበላት አንስተዋል።
ከምክር ቤቱ የጉባኤ አባላት ለተነሱ አስተያየት ማብራሪያ የሰጡት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሪ ጉርሙ ደንን ከውድመት ለመታደግ ግብረ ኃይል በማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፥ በሂደቱ ከጫፍ የወጡ ቀበሌዎችን በመለየትና ቅድሚያ በመስጠት የደን አሰሳ ስራዎች በማከናወን የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል።
በመንገድ ትራንስፖርት ዘርፉ ህብረተሰቡን ለእንግልት መዳረጉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየተፈጠረ በመሆኑ ለመፍትሄ በትኩረት ከሚመለከተው ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ አሪ አብራርተዋል ።
የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመግቢያ ፈተና ውጤት አለማምጣታቸውና የማለፍ ምጣኔን በማሳደግ በኩል ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን ለ11ኛና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች በዩኒቨርስቲ መምህራን የእንግሊዝኛና ሂሳብ ማጠናከሪያ ትምህርት እንደሚሰጣቸውም ተገልጿል።
የጫኝና አውራጅ ማህበር በየቦታው ህብረተሰቡን ለእንግልትና ብዝበዛ በመዳረግ የመልካም አስተዳደር ችግር እየሆኑ በመምጣታቸው የተሰጣቸው እውቅና መነሳቱን ዋና አስተዳደሪው ገልፀው ከግለሰቦች ፍቃደኝነት ውጪ አከናወናለው የሚል አካል በህግ አግባብ ይታያል ብለዋል።
የሸኮ ብሄር ዘመን መለወጫ ቲከሻ ቤንጊ ከጥር 15 እስከ 20 በድምቀት እንደሚከበር የገለፁት አቶ አሪ ህብረተሰቡ ለበዓሉ ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በወረዳው ፍርድ ቤት የሩብ ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት ከምክር ቤቱ የጉባኤ አባላት ለቀረቡት ጥያቄና አስተያየት የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ ምስራቅ ቢያቲ እንደገለጹት ፍርድ ቤቱ ፍትህን ተደራሽ በማድረግ በኩል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝና የማህበራዊ ፍርድ ቤቶችን በማጠናከር ረገድ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በመሀል ሸኮ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የወረዳው ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ የምክር ቤት ጽፈት ቤት እና የአስተዳደር ም/ቤት የ1ኛ ሩብ ዓመት አፈፃፀም ሪፖርትን በጥልቀት በመገመገምና አቅጣጫ በማስቀመጥ ተጠናቋል።
ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
ህዝቡ በግብርና ልማት ሥራዎች የሚያደርገው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የኣሪ ዞን አስተዳደር ገለፀ
ምቹና ለኑሮ ተስማሚ አካባቢ ለመፍጠር የተፈጥሮ ሀብትን መንከባከብ ወሳኝ ነው – የኮሬ ዞን ግብርና መምሪያ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው የከተማ ልማት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን የፎንቆ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ተናገሩ