የሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በስፖርትና ባህል ልማት ዘርፍ የሚገኘውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ አበክሮ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

የሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በስፖርትና ባህል ልማት ዘርፍ የሚገኘውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ አበክሮ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ: ጥር 29/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በስፖርትና ባህል ልማት ዘርፍ የሚገኘውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ አበክሮ መስራት እንደሚገባ የሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እመቤት ወንድሙ ገለፁ።

ቋሚ ኮሚቴው የክልሉን ባህልና ስፖርት ቢሮ የግማሽ ዓመት እቅድ አፈፃፀም ገምግሟል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እመቤት ወንድሙ ተቋሙ ባለፉት 6 ወራት የተሻለ ስራ ማከናወኑን ጠቁመው፥ ስፖርትን ለቱሪዝም ከማዋል ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።

የክልሉን ህዝብ አንድነት በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት፥ በግማሽ ዓመቱ ዝቅተኛ አፈፃፀም የተስተዋለባቸውን ተግባራት ለማሻሻል መትጋት ይገባል ብለዋል።

በክልሉ የሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ሀገር አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ እንዲችሉ የማድረግ ስራ አበክሮ መስራት ያሻል ያሉት ወ/ሮ እመቤት፥ ባህላዊ ቅርሶችን በመጠበቅና በማልማት ለትውልድ እንዲተላለፉ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ኦላዶ ኦሎ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት ባለፉት 6 ወራት በክልሉ የሚገኙ ህዝቦች ክብረ በዓላትና ባህልን ለማስተዋወቅ አፅንኦት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዓላትና የሀገር በቀል እውቀቶችን የማልማትና የማስተዋወቅ ስራ በአፅንኦት እየተሰራ ይገኛል ያሉት ኃላፊው፥ የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ ጊፋታ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ከማድረግ ባሻገር የጋሞ ዱቡሻ ወጋን ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፥ የፎቶና የቪዲዮ መረጃዎችን ለቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ማስረከብ ተችሏል ብለዋል።

የዕደ ጥበብ ምርቶችን ለገበያ የማስተዋወቅ ስራ በስፋት የተሰራ ነው ያሉትአቶ ኦላዶ፥ ከዘርፉም 11 ሚሊዮን 628 ሺህ 600 ብር መገኘቱንም አብራርተዋል።

ባለፉት 6 ወራት ለስፖርት ማህበራት ልማት 1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የተደረገ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፥ 9 የስፖርት ሙያ ማህበራትን ማደራጀት መቻሉንም ተናግረዋል።

በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ ለ2 ሺህ 760 ዜጎች ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መሰራቱን ጠቁመው፥ ከስፖርት ቱሪዝም 17 ሚሊዮን 677 ሺህ 600 ብር እንዲሰበሰብ ተደርጓል።

በግማሽ ዓመቱ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ከ20 በመቶ ወደ 25 በመቶ ማሳደግ መቻሉም ተገልጿል።

በሀገር አቀፍ የስፖርት ውድድሮች በ7 የስፖርት አይነቶች በመሳተፍ 5 ወርቅ ነሃስና ብር ማግኘት ተችሏል ያሉት አቶ ኦላዶ፥ 16 ስፖርተኞች ሀገርን እንዲወክሉ ማስመረጥ ተችሏል ብለዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በቀረበው ሪፖርት ዙሪያ ግልፅነትና ማብራሪያ በሚሹ ጉዳዮች ላይ ጥያቄና አስተያየት ሰጥተዋል::

ዘጋቢ: ዘላለም ተስፋዬ