የጂንካ ማረሚያ ተቋም ታራሚዎች እና የተቋሙ ሠራተኞች የኣሪ ብሔረሰብ ድሽታ ግና ዘመን መለወጫ በዓልን አከበሩ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 30/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጂንካ ማረሚያ ተቋም ታራሚዎች እና የተቋሙ ሠራተኞች የኣሪ ብሔረሰብ ድሽታ ግና ዘመን መለወጫ በዓልን በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል።

የህግ ታራሚዎቹ እንደማንኛውም ማህብረሰብ በዓሉን በተቋሙ እንዲያከብሩ ዕድሉን በማመቻቸቱ ደስተኞች መሆናቸውን ገልፀው፤ በዓሉን ከሁሉም የህግ ታራሚዎች ጋር ማክበራቸውን ተናግረዋል።

ወንጀል በእኛ ይብቃ የሚሉት በዓሉን ያከበሩ የህግ ታራሚዎቹ፤ ለመላው ቤተሰቦቻቸውና የኣሪ ብሔረሰብ፣ ወዳጆች እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያንውያን በዓሉ የሠላም፣ የፍቅርና የአብሮነት እንዲሆን ተመኝተዋል።

የጂንካ ማረሚያ ተቋም አዛዥ ምክትል ኮማንደር አስቻለው ነሬሬ በበኩላቸው፤ ተቋሙ ከየአካባቢው በተለያየ የወንጀል ፍርደኛ የሆኑ የህግ ታራሚዎች ጋር የኣሪ ብሔረሰብ ድሽታ ግና የዘመን መለወጫ ክብረ በዓል ማክበር መቻሉን ገልፀዋል።

መታሰር መታረም እንጅ የሕይወት ፍፃሜ አይደለም ያሉት ምክትል ኮማንደር አስቻለው፤ ሁሉም ህዝብ ከወንጀል በመቆጠብ በሰፊው ልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

በዓሉን የህግ ታራሚዎችና የተቋሙ ሠራተኞች እሴቶቹን በጠበቀ መልኩ እንዲያከብሩ እንደተደረገና ለመላው የበዓሉ ባለቤት ኣሪ ብሔረሰብ እና ለኢትዮጵያውያን እንኳን ለ9ኛ ጊዜ በአደባባይ ለሚከበረው ድሽታ ግና በዓል አደረሰን አደረሳችሁ ብለዋል።

በመርሐ ግብሩ የተገኙት የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ፤ ተቋሙ በቅጥር ግቢ በዓሉ እንዲከበር በማድረጉ አመስግነዋል።

ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች የህግ ታራሚዎችን በመቀበል የሚያስተናግደው የጂንካ ማረሚያ ተቋም፤ የታራሚዎች አያያዙን በተሻለ መልኩ ይዞ እየሠራ የሚገኝ በመሆኑ ለተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች በዞኑ ሕዝብ ስም አመስግነዋል።

ዘመን መለወጫ በዓሉ ነገ በጂንካ ሁለገብ ስታዲየም ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበር ታውቋል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን