ሀዋሳ፡ ታህሳስ 01/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለዘመናት የቆየውን የሰላምና የመከባበር ባህል ለማስቀጠል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል።
በኮሬ ዞን ኬሌ ከተማ አስተዳደር የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምስረታ ተካሂዷል።
በምስረታው ጉባኤ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በኮሬ ዞን የኬሌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ዮሐንስ ኃይሉ እንደተናገሩት፤ ቀጣይነት ያለውን ዕድገትና ሰላም ለማረጋገጥ ከተፈለገ የመከባበር፣ የመቻቻልና የአብሮነት ባህላችንን በማስፋት ልዩነታችንን እያጠበብን መሄድ አለብን።
የሃይማኖት ተቋማት በጋራ ተቀራርበው ከመሥራት ባሻገር በተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ በመሳተፍ የራሳቸውን መልካም አሻራ እንዲያሳርፉ ከማድረግ ረገድ የሚመሠረተው ጉባኤ ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል።
የኬሌ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ ኢንስፔክተር የጌታነህ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ የሃይማኖት ተቋማት ለዘመናት የቆየውን አብሮነት ለማስቀጠልና በመካከላቸው ልዩነቶች እንዳይፈጠሩ ለማድረግ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።
በሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምስረታ ላይ ለቀጣይ ሁለት ዓመታት የኬሌ ከተማ አስተዳደር ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሚመሩ ኃላፊዎች ምርጫም ተካሂዷል።
አቶ መሰለ አጋፋሪ እና ቄስ ምህረት ጋሌ የጉባኤው ዋና እና ምክትል ሰብሳቢ ሆነው የተመረጡ ሲሆን በተለይም በእምነት ተቋማት ልዩነቶችና አለመግባባቶች እንዳይፈጠሩ በማድረግ በልማትና በማህበራዊ ሥራዎች ከመንግሥት ጎን በመቆም እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።
የተሰጠንን ትልቅ ኃላፊነት በጋራ እንድንወጣ ምዕመናን በፀሎትና በሚያስፈልገው ሁሉ ከጎናችን ሊቆሙ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ ለምለም ኦርሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
ትምህርት የሀገርን ኢኮኖሚ ከመገንባት ባለፈ በራስ የሚተማመን ዜጋ ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተገለጸ
ከልጅነቴ ጀምሮ የግብርና ሥራ ሱሴ ነው ! ማሳዬን በቀን ሦስት፣ አራት ጊዜ ካልጎበኘሁኝ ያመኛል – ሞዴል አርሶአደር አቶ ኮቾ ከተማ
የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ ዙር የከፍተኛና መካከለኛ የአመራሮች ስልጠና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መሰጠት ጀመረ