“ጉንፋን በአንቲባዮቲክስ መድሀኒቶች አይታከምም” – ዶክተር ሚስጥር አወቀ
በገነት ደጉ
የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን ዶክተር ሚስጥር አወቀ ይባላሉ፡፡ በሀዋሳ ከተማ በሚገኘው ያኔት የመጀመሪያ ደረጃ የግል ሆስፒታል የህፃናት ስፔሻሊስት እና በይርጋለም ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህር ናቸው፡፡ ለአምስት ዓመታት በህፃናት ስፔሻሊስትነት እንዲሁም ተጨማሪ አምስት ዓመት በመምህርነት በጠቅላላው በህክምና ሙያ ለ10 ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡ የህፃናት የመተንፈሻ አካላት በሽታ መበራከት ምክንያቶች፣ በህፃናት የተለመደ ጉንፋን እና ጉንፋንን በቤት ውስጥ ማከም ይቻል ይሆን? በሚሉ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከእርሳቸው ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
ንጋት፡- በቅድሚያ ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑ እናመሰግናለን!
ዶክተር ሚስጥር፡- እኔም እንግዳችሁ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ!
ንጋት፡- ከልጅነት ጀምሮ ያለው የትምህርት ዓለም ጉዞዎን በማንሳት እንጀምር?
ዶክተር ሚስጥር፡- ተወልጄ ያደኩት እዚሁ ሀዋሳ ልዩ ስሙ ማውንቴን ስናክ ተብሎ በሚታወቀው ሰፈር ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን ማውንትኦሊቭ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ተከታትያለሁ፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በኤስ.ኦ.ኤስ ትምህርት ቤት ተከታትዬ በ2000 ዓ.ም ትምህርቴን አጠናቅቄያለሁ፡፡
ወደ ከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ስውስድ በወቅቱ ከ500 ነጥብ 470 በማምጣት በ2ዐዐ1 ዓ.ም ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በህክምና ሙያ ትምህርቴን ተከታትዬ በ2006 ዓ.ም ተመረቅኩኝ፡፡ በተማሪነቴም ጎበዝ እና የደረጃ ተማሪ ነበርኩ፡፡
ስራ የጀመርኩት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ነው። በመምህርነት ለአንድ ዓመት ካገለገልኩ በኋላ ይርጋዓለም ወደሚገኘው ይርጋዓለም ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በመዘዋወር ማገልገል ጀመርኩ፡፡
በመቀጠልም ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በመግባት በህፃናት ህክምና ስፔሻላይዝ በማድረግ ተመርቄያለሁ፡፡
የስፔሻሊቲ ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ በይርጋለም ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ላይ በመምህርነት በትርፍ ሰዓቴ ደግሞ በያኔት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በህፃናት ስፔሻሊስትነት እና ረዳት ፕሮፌሰር በመሆን እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡
በህፃናት ስፔሻሊስትነት ለአምስት ዓመታት ያህል ሰርቻለሁ፡፡ በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ። ከልጅነት ጀምሮ በህክምናው በተለይም በህፃናት ህክምና ላይ መስራትን እመኝ ነበር፡፡ እሱን በማሳካቴ ደግሞ ደስተኛ ነኝ፡፡
ንጋት፡- ወደ ህክምናው እንምጣና እስቲ ጉንፋን ምንድነው?
ዶክተር ሚስጥር፡- ጉንፋን ማለት የላይኛው የመተንፈሻ አካልን የሚያጠቃ በቫይረስ የሚመጣ ሕመም ነው፡፡ ይህም ማለት በፀረ-ተዋሲያን የሚተላለፍ ኢንፌክሽን ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ የሚያመጡ ፀረ- ተህዋሲያን ወይም ቫይረሶች ናቸው፡፡ ብዙ ዓይነት ቫይረሶች አሉ፡፡ ለአብነትም እነ ኮረና እና የተለያዩ የቫይረስ ዓይነቶች በህክምናው ዘርፍ አሉ፡፡ ብዙ ዓይነት የቫይረስ ምክንያቶች ቢኖሩትም ከሰዎች ወደ ሰዎች ግን በቀላሉ ይተላለፋሉ፡፡
በህፃናት እና በአዋቂዎች ላይ ቫይረሶቹ ወይም ፀረ-ተህዋሲያኖቹ ሊለያዩ አይችሉም፡፡ ግን ለሰውነት የሚሰጡት ምላሽ የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ የመጀመሪያው ከህፃናት ዕድገት ጋር ተያይዞ ሊሆን ይችላል፡፡
ንጋት፡- ለጉንፋን መከሰት መንስኤዎች ምንድን ናቸው?
ዶክተር ሚስጥር፡- መንስኤዎች በቫይረሶች ምክንያት ነው፡፡ በአብዛኛው ጊዜ ሰዎች በንጽህና ጉድለት፣ ለምሳሌ ለህፃናት ዳይፕር በቶሎ ሳይቀይሩ መቆየት የሚሉ ብዙ ምክንያቶችን ለጉንፋን እንደ ምክንያት ያቀርባሉ፡፡ በህክምናው ሙያ ግን ጉንፋን መተላለፊያ መንገዶችን ብሎ ያስቀመጠው በቫይረስ ብቻ እና ብቻ ነው፡፡
ንጋት፡- መተላለፊያ መንገዶችስ ምንድናቸው?
ዶክተር ሚስጥር፡- አንድ ሰው ጉንፋን ከተያዘ በኋላ ሲያስል፣ ሲያስነጥስ፣ እጅን ባለመታጠብ እንዲሁም ባስነጠሰበት እና ባሳለበት እጅ ንክኪ ሲኖር በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፍ ይችላል። ዋናው መተላለፊያ መንገድ የፈሳሽ ቅንጣቶች ናቸው፡፡
በተለይም እናቶች በመጥፎ ሽታ ጉንፋን ይተላለፋል ብለው ያምናሉ፡፡ ለህፃናት ንጽህና የራሱ የሆነ ጥሩ ነገር ቢኖረውም እንኳን በህክምናው መጥፎ ሽታ ከጉንፋን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም፡፡
ማንኛውም ሰው በጉንፋን ከተያዘ ህፃናትን መሳም፣ መነካካት፣ ህፃናት ላይ መሳል አያስፈልግም፡፡ ህፃናትን ጉንፋን ቢይዛቸውም ሆነ ባይዛቸው የንፅህና ጉዳይ ሌላ ጉዳይ እንጂ ከዚያ ጋር ምንም ዓይነት ቀጥታ የሆነ ግንኙነት የለውም።
ንጋት፡- ምልክቶቹስ ምን ይሆኑ?
ዶክተር ሚስጥር፡- ምልክቶቹ ማስነጠስ፣ አፍንጫ ማሳከክ፣ በአፍንጫ ፈሳሽ መውጣት፣ ማዝረክረክ እንዲሁም ትኩሳት ዋና ዋና ምልክቶች ናቸው፡፡
ንጋት፡- ጉንፋን ከልጅ ልጅ የበሽታው ሁኔታ ይለያያል፤ ምክንያቱስ ምን ይሆን?
ዶክተር ሚስጥር፡- እውነት ነው ከህፃናት ህፃናት ይለያያል፡፡ ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው፡፡ የበሽታ መከላከል አቅም ከአንድ ህፃን ሌላ ህፃን ላይ ይለያያል፡፡ ህፃናት በተፈጥሮ ይዘዋቸው የሚወለዱ በርካታ በሽታዎች ሊኖሩ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የሳምባ ምች፣ አስም፣ የልብ ክፍተቶች፣ የመተንፈሻ አካላት አለርጂዎች አሉ፡፡ እነዚህ በተፈጥሮ ይዘው የተወለዱ ህመሞች ካሉ ጉንፋን ይባባሳልም፤ ተጋላጭነታቸውንም ሰፊ ያደርጋል፡፡
ከላይ የጠቀስናቸው ህመሞች ከሌሉባቸው ጉንፋን ቢያዙ እንኳን አይወሳሰብባቸውም። ይህም ማለት ከእነዚህ ህመሞች ጋር የተወለዱ ህፃናት ጉንፋን ከያዛቸው ብዙውን ጊዜ ወደ ሳምባ ምች የመቀየር ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡
መደበኛ ጉንፋን የተያዙ ልጆች ከ3 እስከ 5 ቀናት ውስጥ ለውጥ ይኖራቸዋል፡፡ በተለይም ቤተሰብ ከ5 ቀናት በላይ የሆኑ የጉንፋን ምልክቶች በህፃናት ላይ ካሉ እና የአተነፋፈስ ሁኔታ ትክክል ካልሆነ ወደ ሳምባ ምች ሳይቀየር ህፃናቱን ቤት ይዘዋቸው ከማቆየት ይልቅ ወደ ህክምና ተቋማት በመውሰድ እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ የተሻለ ነው፡፡
ንጋት፡- ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት ገዳይ የሚባሉ የትኛዎቹ በሽታዎች ናቸው?
ዶክተር ሚስጥር፡- የዓለም ጤና ድርጅት ከአምስት ዓመት በታች ላሉ ህፃናት ገዳይ በሽታዎች ብሎ ከለያቸው አምስት ህመሞች መካከል ካለጊዜ መወለድ /አንድ ህፃን ከ37-38 ሳምንት መወለድ/ ሲሆን ከዚያ ጊዜ ቀድሞ የተወለዱ ህፃናት ተያያዥ ችግሮች ይኖርባቸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የመተንፈሻ አካላት ችግር፣ ኢንፌክሽን እንዲሁም ብዙ ተያያዥ ችግሮች አሉት። ከዚህም ጋር ተያይዘው ሚመጡ ህመሞች ገዳይ ናቸው ተብሎ ይወሰዳል፡፡
ሁለተኛው እናትየው ረጅም ምጥ ላይ እያለች ህፃኑ ታፍኖ ከሆነ ራሳቸው ይዘዋቸው የሚመጡት የጎንዮሽ ጉዳት አላቸው፡፡ በዚህን ጊዜ በህፃናቱ ላይ ቋሚ የሆነ የጭንቅላት ጉዳት ሊያመጣባቸው ይችላል፡፡
ሌላው ብዙውን ጊዜ ምጥ የበዛባቸው እናቶች በሽርት ውሃ መታፈንና መጠጣትም እንዲሁም እናት በወሊድ ጊዜ ብዙ ደም መፍሰስ ህፃናትን ለሞት ሊዳርጋቸው ይችላል ማለት ነው፡፡
ሶስተኛው ደግሞ የሳምባ ምች (ኒሞኒያ) የምንለው ሲሆን አራተኛው ተቅማጥ እንዲሁም ሲወለዱ በሚፈጠሩ ችግሮች የልብና የሳምባ አፈጣጠር ችግርች ህፃናትን ለሞት ሊዳርጉ የሚችሉ ህመሞች ናቸው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው በጣም ዘግይተው የሚወለዱ ልጆችም እንዳሉ ታሳቢ በማድረግ ያም ሌላ የተለያዩ ችግሮች እንዳሉት እና የራሱ የሆነ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለውም ታሳቢ ልናደርግ ይገባል፡፡
ንጋት፡- ጉንፋንን በቤት ውስጥ ማከም ይቻል ይሆን?
ዶክተር ሚስጥር፡- አዎ ማከም ይቻላል። በቫይረስ ቅንጣት የሚተላለፍ ህመም በመሆኑ አወሳሳቢ ሁኔታዎች ከሌሉ በስተቀር ማከም ይቻላል፡፡ በህክምናውም ለጉንፋን ተብሎ የሚሰጥ መድሀኒት የለም፡፡ በተለምዶ ህብረተሰቡ ከህክምና ባለሙያዎች የሚወስዳቸው የማይመከሩ አንቲባዮቲክሶች የራሳቸው የጎንዮሽ ጉዳት አላቸው፡፡ ጉንፋን ቫይረስ በመሆኑ የቤት ውስጥ ድጋፍ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
ሌላው በተለይም ለህፃናትም ሆነ ለአዋቂዎች እቤት ውስጥ በፈላ ውሃ እና ትንሽ ጨው በመጠቀም እስቲም ማድረግ ነው፡፡ በሌላ ጎኑ በተለይም ቫይታሚን ሲ ያላቸውን ለምሳሌ የፍራፍሬ ጭማቂ፣ የማር ጭማቂ፣ ወተት እና እነዚህን ምግቦች ቀድሞ ከተለመደው መጠናቸውን በመጨመር ቶሎ ቶሎ በደንብ መስጠት ለመከላከል ሂደቱ ሊያግዝ ይችላል። በአማካይ ቀለል ያለ ጉንፋን ከ5 አስከ 7 ቀናት የሚቆይ ሲሆን ምልክቶቹ ከቆዩ ወደ ህክምና ተቋም መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉም ጉንፋን በህክምና ተቋም ይታከማል ማለት አይደለም፡፡
በእነዚህ ቀናት ከመሻሻል ይልቅ መባባስ ካለ ግን ወደ ህክምና በመውሰድ የባለሙያ ድጋፍ ማግኘት ይገባል፡፡ በተለይም በጉንፋን ወቅት ላይ ለህፃናትም ሆነ ለአዋቂዎች የአመጋገብ ስርዓትን ማስተካከልና እረፍት መውሰድ ይመከራል፡፡ ይህም የበሽታ መከላከል አቅማቸውን እንዲጨምር ያደርጋል፡፡
ንጋት፡- ህፃናት በተደጋጋሚ በጉንፋን የሚያዙበት ምክንያቶችስ ምን ሊሆኑ ይችላሉ?
ዶክተር ሚስጥር፡- የጤና ሁኔታዎች ከህፃናት ህፃናት ይለያያል፡፡ ጉንፋን የመያዙ ብቻ ሳይሆን የመከላከል አቅማቸውም ይለያያል፡፡ በተለይም አስም ያለባቸው ህፃናት፣ የልብ ክፍተት ያለባቸው፣ ሳንባቸው ላይ ችግር ያለቸባቸው ህፃናት እንዲሁም የበሽታ መከላከል አቅማቸው ዝቅ ያሉ ህፃናት ከሌሎቹ ቶሎ ቶሎ የመያዝ ሁኔታዎች እና ኤች.አይ.ቪ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው ህፃናት የመያዝ ዕድላቸው ይጨምራል፡፡
ብዙውን ጊዜ የተለያዩ ችግሮች ያሉባቸው ህፃናት ከሌሎች ህፃናት በጣም የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ስለዚህ የበሽታ የመከላከል አቅም ከተለያዩ የጤና ችግሮች ጋር ባሉ ልጆች ላይ ይለያል ማለት ነው፡፡
ንጋት፡- የመከላከያ መንገዶችስ ምንድ ናቸው?
ዶክተር ሚስጥር፡- ወላጆች ልጆቻቸውን በአግባቡ መያዝ፣ እጃቸውን ቶሎ ቶሎ መታጠብ እና ሳኒታይዝ ማድረግ፣ የአፍንጫ እና የፊት መሸፈኛ በትክክል መጠቀም እንዲሁም በኮሮና ቫይረስ ወቅት የምናደርጋቸውን ቅድመ ጥንቃቄዎችን በሙሉ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
እንዲሁም የበሽታ መከላከልን ሊያጎለብቱ የሚችሉ ምግቦችን መውሰድ ይገባል፡፡ በተለይም ሌሎች ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸውን ህፃናት ጉንፋን ነው በማለት እቤት ውስጥ ማቆየት ግን አይመከረም፡፡
ብዙውን ጊዜ የተመጣጠነ ምግቦችን ለህፃናት በመስጠት የበሽታ መከላከል አቅማቸውን መጨመር ከማንኛውም እናቶች የሚጠበቅ የዕለት ተዕለት ተግባር መሆን አለበት፡፡ ለህፃናት በተለይም ከሁሉም ዓይነት ምግቦች ከጥራጥሬ፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ እና ሌሎችንም የምግብ ዓይነቶችን በትክክል መስጠት ዋናው የመከላከያ መንገዶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡
በተለይም ለበሽታ ተጋላጭ ናቸው ብለን ያልናቸውን ልጆች በተለየ ሁኔታ እንክብካቤ ማድረግ ለጉንፋን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ዓይነት በሽታዎች ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ መታወቅ ያለበት አስም እና አለርጂ ያለባቸው ህፃናትን በተለየ ሁኔታ ጥንቃቄ ካልተደረገላቸው ለሳምባ ምች እና ለጉንፋን ተጋላጭ በመሆናቸው የተለየ እንክብካቤ እና ድጋፍን ይፈልጋሉ፡፡
አለርጂ ያለባቸው ልጆች በተለየ ለጉንፋን ተጋላጭ በመሆናቸው የቤት እንስሳት ማለትም ውሻ፣ ድመት፣ ብናኝ እና ሽታ ያላቸውን ነገሮች ማራቅ ያስፈልጋል፡፡ ለአለርጂ መጥፎ ሽታዎችን ብቻ ሳይሆን ጥሩ ሽታዎች ስለሚቀሰቅሱ መጠንቀቅ እና ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ንጋት፡- ልጆችን ከትምህርት ቤት ያስቀረው የሰሞኑ ጉንፋንስ ምን ይሆን?
ዶክተር ሚስጥር፡- ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ጉንፋን መነሻዎቹ ቫይረስ እና የቫይረስ ቅንጣቶች ናቸው፡፡ በእርግጥ በዚህ ወቅት የመጣውን ቫይረስ በጤና ጥበቃ ደረጃ ተጠንቶ ካልሆነ ይህ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን በጣም በተደጋጋሚ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑ ህፃናት ህክምና ተቋማት መጥተው የተስተናገዱበት የበሽታ ኬዞች አሉ፡፡
ወረርሽኙ አለ ወይ? ለሚለው አዎ መልሳችን ሲሆን የቫይረሱ ዓይነት ግን በጥናት የተደገፈ እና የታወቀ አይደለም፡፡
ንጋት፡- የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት?
ዶክተር ሚስጥር፡- ሰሞኑን የነበሩ ጉንፋኖች እንደ ወረርሽኝ ናቸው፡፡ ሌላ አዲስ ቫይረስ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለ። ራሱ ኮቪድም ሊሆን ስለሚችል ጥንቃቄ ማደረግ ክፋት የለውም፡፡
በትምህርት ቤት እንደ ወረርሽኝ ለሚታየው ጉንፋን ምክንያቱ አብሮ መጫወት እና በአንድ ክፍል ብዙ ተማሪዎች መኖር ሊሆን ይችላል፡፡
በዚህም ልጆቻችሁን የእጃቸውን ንጽህና እንዲጠብቁ፣ የአፍንጫ እና የአፍ መሸፈኛ እንዲያደርጉ እንዲሁም በቤት ውስጥ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እና ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ እንደ ቤተሰብ ግን በምግብ መደገፍ እና ጥንቃቄን ለልጆች ማድረግ አስፈላጊነቱ የጎላ ነው፡፡
እንደ አንድ ባለሙያ ግን የማስተላልፈው በቤት ውስጥ ቤተሰቦች የተለያዩ አንቲባዮቲክስ መድሀኒቶችን መስጠት አስፈላጊ አለመሆኑን እና አንቲባዮቲክሱ የሳንባ ምችን ይዞ ስለሚመጣ ምንም ዓይነት መድሀኒቶችን በቤት ውስጥ መስጠት አስፈላጊ አለመሆኑን ሊረዱ ይገባል፡፡
አብዛኛው ቤተሰብ ከፋርማሲ የተለያዩ አንቲባዮቲክሶች በመግዛትና በመጠቀም ከአቅም በላይ ሲሆን ወደ ህክምና ተቋም ስለሚያመጡ ከዚያን በኋላ ያለውን ህክምና ውስብስብ ያደርገዋል፡፡ በአጠቃላይ ጉንፋን ቫይረስ በመሆኑ በአንቲባዮቲክስ እንደማይታከም መታወቅ አለበት፡፡ ለባክቴሪያ የሚሸጡ መድሀኒቶች በቫይረስ የሚተላለፉ በሽታዎችን ስለማያድኑ ይህንን መረዳት ያስፈልጋል የሚል መልዕክት አለኝ፡፡
ንጋት፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሠግናለሁ፡፡
ዶክተር ሚስጥር፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
More Stories
“የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና በማጉላት አካታችና ዘላቂ ልማትን እናረጋግጣለን!”
እርቅ
የአምራች ዘርፉን የመቀላቀል ውጥን