ሆስፒታሉ ስራውን ለማዘመንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የኤም አር አይ ማሽን ማስመጣቱንም አስታውቋል።
አርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የአጎራባች ክልሎችንና ዞኖችን ጨምሮ ለአካባቢው ማህበረሰብ አግልግሎት እየሰጠ ዘልቋል።
ይህን አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን (MRI) ማግኔቲክ ሪዞናንስ እሜጂንግ ማሽን ማስመጣቱን የአርባምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶ/ር አምባቸው ዱማ ተናግረዋል።
የማሽኑ መምጣት ስራውን ከማቀላጠፍ ባለፈ ከዚህ በፊት የማይሰጡ የደረትና የጭንቅላት አካባቢ ህመሞች ህክምና እዚሁ ሊሰጥ እንደሆነም አሳውቀዋል።
ከዚህ በፊት የዚህን ማሽን ግልጋሎት ለማግኘት ወደ ሌላ አካባቢ በመንቀሳቀስ ላልተፈለገ ወጪና እንግልት ይዳረግ የነበረውን ህዝብ ለመታደግ ከቻይና ባለሀብቶች ጋር በጋራ ከ100 እስከ 150 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚያወጣ መሣሪያ ማስመጣት መቻሉን ጠቁመዋል።
የአርባምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አዲሱ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ የመጣው (MRI) አጠቃላይ የሰውነት ክፍልን፣ ጭንቅላትና ልብን ጨምሮ በማግኔቲክ ሪዞናንስ እነርጂ አማካይነት ምርመራ የሚያደርግ እንደሆነ አብራርተዋል።
የሆስፒታሉ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ህክምናና የቀዶ ህክምና ክፍል ሀላፊ እንዲሁም ምክትል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር በጋሻው መለሰ፤ አርባምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል በአገር ደረጃ የመጀመሪያ አልትራ ሳውንድ ምርመራ የተደረገበት ሆስፒታል መሆኑን አስታውሰው (MRI) ማሽን ወደ ሆስፒታሉ መምጣቱ የብዙ ማህበረሰብ እንግልት እና ያልተፈለገ ወጪ እንደሚቀረፍ አስታውቀዋል።
ዘጋቢ፡ ባደገ በልሁ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን

More Stories
የሰራተኞች የገንዘብ ቁጠባ እና ብድር ኅብረት ሥራ ማህበር ብዙዎችን የቤት ባለቤት ማድረጉ ተገለጸ
በሁሉም ዘርፎች እንደሀገር አመርቂ ውጤቶች እየተዘመገቡ ነው – የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርዓትን በማዘመን የመረጃ ታማኝነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ