የወባ በሽታ ስርጭትን የመከላከልና የመቆጣጠርን ጉዳይ ቀዳሚ ተግባር አድርጎ እየሰራ መሆኑን የስልጤ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ

በዞኑ ሁልባረግ ወረዳና የአለም ገበያ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ ከበሽታው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለመጠበቅ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

የክረምቱ ወራት መጠናቀቁን ተከትሎ የስርጭት መጠኑ ከፍ የሚለውን የወባ በሽታ ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የስልጤ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሸምሴ ኸይረዲን ተናግረዋል።

በተለይም በዞኑ 13 ወረዳዎች ለወባ በሽታ ስርጭት ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቁመው ይህንን የስርጭት መጠን ለመቀነስ ማህበረሰቡ የመከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ በሽታውን የመቆጣጠር ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዞኑ የስርጭት መጠኑ ከፍ ያለባቸው አራት ወረዳዎች ተለይተው የኬሚካል ርጭት የተጀመረ መሆኑን ያነሱት አቶ ሸምሴ፤ ሌሎችም የወባ በሽታ መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ በተሰራው ስራ የበሽታው የስርጭት መጠን እየቀነሰ መሆኑን አንስተዋል።

በዞኑ በተለይም ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ስራዎች የተቆፈሩ ጉድጓዶችና እና በተፈጥሮ ሀይቆች አካባቢ ያሉ ወረዳዎች ለወባ በሽታ ስርጭት ተጋላጭ መሆናቸውን ያነሱት ኃላፊው፤ በውሃማ አካባቢዎች የወባ በሽታ ትንኝ እንዳትራባ የመከልከልና ኬሚካል የመርጨት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሚፈለገው ልክ ባይሆንም እየቀረበ ያለው የወባ በሽታ መከላከያ ግብዓቶችን ማህበረሰቡ ጋር በማድረስ በአግባቡ እንዲጠቀሙ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ አስፈላጊው ክትትል እንደሚደረግ አንስተዋል።

እንደ ሀገርም ከወባ በሽታ መድኃኒት አቅርቦት እጥረት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ችግር እንዳለ ሆኖ የቀረበውን የወባ በሽታ መድኃኒት በአግባቡ ለታማሚው ከማድረስ ጋር ተያይዞ ቅሬታ እየተነሳበቸው የነበሩ አካላት ላይ የማስተካከያ እርምት እንደተወሰደ አቶ ሸምሴ ተናግረዋል።

የሁልባራግ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙስባ ሰይድ እና የአለም ገበያ ከተማ አስተዳደር ጤና ዩኒት የበሽታ መከላካልና መቆጣጠር የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ኑርታታ መሀመድ በጋራ እንደገለጹት፤ በወረዳውና በከተማ አስተዳደሩ የወባ በሽታ ስርጭት የመከላከል ስራዎች በትኩረት እየተሰሩ እየተሰሩ ነው።

የአካባቢ ንጽህና ከመጠበቅ ባለፈ ውኃ የሚያቁሩ ቦታዎችን የማፋሰስ እና የማዳፈን ስራ በመስራት ማህበረሰቡ ራሱን ከወባ በሽታ እንዲጠብቅ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ገልፀዋል።

በተጨማሪም የአጎበር አቅርቦት በሚፈለገው ልክ ባይሆንም የቀረበውን ያህል በማሰራጨት ማህበረሰቡ በአግባቡ እንዲጠቀም የማድረግ ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት።

በሁልባረግ ወረዳ የስርጭት መጠኑ ከፍ ያለባቸው ቀበሌያት ተለይተው የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ ሲሆን በዚህም የበሽታው ስርጭት መጠን እየቀነሰ መሆኑን አቶ ሙስባ ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን የሰጡን የሁልባረግ ወረዳና የአለም ገበያ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ የወባ በሽታ ስርጭት መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ ከበሽታው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለመጠበቅ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘጋቢ: አሚና ጀማል – ከሆሳዕና ጣቢያችን