“የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና በማጉላት አካታችና ዘላቂ ልማትን እናረጋግጣለን!”

በመለሠች ዘለቀ

የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን እጩ ዶክተር ሁሪያ አሊ ይባላሉ፡፡ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ናቸው፡፡  እንደ  ሀገር አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ከማድረግ ረገድ የተሰሩ ስራዎችንና ተያያዥ ጉዳዮቸን በማንሳት ቆይታ አድርገናል፡፡

ንጋት፡ለቃለ መጠይቃችን ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሠግናለሁ፡፡

እጩ ዶክተር ሁሪያ አሊ፡ እኔም ስለተሰጠኝ እድል አመሠግናለሁ፡፡

ንጋት፡–  በትውውቅ እንጀምር?

እጩ ዶክተር ሁሪያ አሊ፡ የተወለድኩት በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ነው፡፡ አድገቴ አዲስ አበባ ሲሆን የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተከታትያለሁ፡፡ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተመልሼ ወደ መቀሌ ሄድኩኝ፡፡ ከዚያም የመጀመሪያ ዲግሪዬ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ተከታትያለሁ፡፡ ሁለተኛ ዲግሪዬን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ”ሂዩማን ኢን ኢኮኖሚክስ ዴቨሎፕምንት” አግኝቻለሁ። የሶስተኛ ዲግሪዬን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ “ሞቢሊቲ ኤንድ ሲትዚን ሺፕ” እያጠናሁ እገኛለሁ፡፡

ተማሪም ሆኜ በተለያዩ ስራዎች ላይ እሳተፍ ነበር፡፡ ለአብነትም ቋንቋ በማስተማር፣ ተማሪዎችን በማስጠናት እና ከማህበራዊ ጉዳዮች ጋር የሚገናኙ ተግባራት ላይም እሳተፍ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ስራዬ መምህርነት ሲሆን በተለያዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አስተምሬያለሁ፡፡ በመቀጠልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በተለያዩ የግልና የመንግስት ኮሌጆች ላይ አስተምሬያለሁ፡፡

በተለያዩ ተቋማት ላይ በኃላፊነት ሰርቻለሁ፡፡ በትምህርት ሚኒስቴር ላይ ሚኒስተር ዴኤታ ነበርኩ፡፡ ኢኖቭሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስተር ዴኤታ ሆኜ አገልግያለሁ፡፡ አሁን ላይ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስተር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሆኜ እያገለገልኩ እገኛለሁ፡፡

ንጋት፡ሴትነትና አመራርነት እንዴት ይጣጣማሉ?

እጩ ዶክተር ሁሪያ አሊ፡ ሴትነትና አመራርነት በደንብ ይጣጣማሉ ብዬ ነው የምመለከተው፡፡ ምንክያቱም የሴት ልጅ አመራርነት የሚጀምረው  ከቤት ነው፡፡ ልጅ ስትሆን ከእናቷ እየተማረች የማደግ ሁኔታ አለ፡፡  ወጣት ስትሆን እናቷን የማገዝ ኃላፊነት አለባት፡፡ እናት ስትሆን ደግሞ ትዳሯን፣ ልጆቿን እና ቤቷን የማስተዳደር ኃላፊነት የሴቷ ነው፡፡ ያላትን ገቢ በጥበብ አጣጥማ ቤቷን መምራት ትችላለች፡፡

ስለዚህ አመራርነት ለሴት ልጅ አዲስ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ከታች ጀምራ ይዛ የምትመጣው ልምድ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡  ለዚያም ነው ሴቶች አመራርነት ላይ ሲቀመጡ ውጤታማ የሚሆኑት፡፡  አመራርነት ብዙ ጊዜ ማቀናጀት ይፈልጋል። ሴቶች ደግሞ የማቀናጀት ልምድ አላቸው። ስለዚህ ሴትነትና አመራርነት አብረው የሚሄዱ፥ እጅና ጓንት ናቸው፡፡

ንጋት፡አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደ ሀገር እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን እንዴት ይገልጿቸዋል?

እጩ ዶክተር ሁሪያ አሊ፡ እንደ ሀገር አካል ጉዳተኝነትን ታሳቢ ያደረጉ ስራዎች መሰራት አለባቸው በሚል ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች እየቀረጽን እንገኛለን፡፡ ደንቦችንም እያዘጋጀን ነው፡፡ አካል ጉዳተኞች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚሰሩ በርካታ ስራዎች አሉ፡፡ በተለይም ብሄራዊ ማህበራዊ ጥበቃ ላይ አካል ጉዳተኞች ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል ማለት ነው፡፡

ይህንን ስራ ስንሰራ ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ነው፡፡ በተለይ ትምህርት ቤቶች አካል ጉዳተኝነትን እንዲያካትቱ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሰራሽ ምክንያት  ለሚከሰት አካል ጉዳት በመጀመሪያ አክሞ የማዳን ተግባራት ይከናወናል፡፡ አካል ጉዳተኝነት ውስንነት ሳይሆን ልዩ ተስጥኦ እንደሆነ ማህበራዊ ንቅናቄዎችን በማድረግ ወደ ትምህርት ስርዓት እንዲመጡ ፥ እንዲማሩ የማድረግ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር እና የስራ እድል እንዲያገኙ ለማስቻል በርካታ ተግባሮች ተከናውነዋል፡፡

ሌሎች ባለድርሻ አካላትም አካል ጉዳተኞችን ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠሩላቸው ይደረጋል፡፡ በተለይ ህንጻዎች ሲገነቡ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ ማድረግ አለባቸው፡፡

ለአካል ጉዳተኞች ግንዛቤ የሚፈጥሩና ጥቅሞቻቸው እንዲከበሩ ጥረት የሚያደርጉ ማህበራትን በገንዘብና በቴክኒክ እንደግፋለን። በየአመቱ የተለያዩ ክልሎች ጋር በመሄድ ስራዎች ይሰራሉ፡፡

አካል ጉዳተኝነት ትኩረት ይፈልጋል። በተለይ ኢትዮጵያ የምትመራበት ፖሊሲ እንደ ሀገር አካታች የሆነ ብልጽግናን ማረጋገጥ ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ ሁሉንም ዜጋ እኩል ተጠቃሚ እና ተሳታፊ ማድረግ ሲቻል ነው፡፡

አካል ጉዳተኝነት ማለት ውስንነት ሳይሆን ልዩ ችሎታ ይዞ መውጣት እንደሆነ አምኖ የስራ፥ እድሎችን መፍጠር ላይ ሁሉም አካላት በርብርብ መስራት ከቻለ፥ ልማታችንን ማረጋገጥ እንችላለን፡፡

ንጋት፡በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በነበሩ ጦርነቶች ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን የመደገፍ ስራ ምን ይመስላል?

እጩ ዶክተር ሁሪያ አሊ፡ ጦርነቶች ሲኖሩ ከሚከሰቱ ችግሮች አንዱ አካል ጉዳተኝነት ነው፡፡ አካል ጉዳተኝነት በጦርነት ምክንያት ሲከሰት በቅድሚያ ህክምና እንዲያገኙ በማድረግ ጤንነታቸውን ማረጋገጥ ነው። ለዚህም ከጤና ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እንሰራለን፡፡

በመቀጠል የትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እንሰራለን፡፡ ማህበራዊ ጥበቃዎች ይደረግላቸዋል፡፡

እንደ ሀገር በሰው ሰራሽ ምክንያት አካል ጉዳተኝነት እንዳይፈጠር የመከላከል ስራዎች ላይ እናተኩራለን፡፡ በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሰራሽ ምክንያት ጉዳት ለሚያጋጥማቸው ህክምናን በማስቀደም ሌሎች ተጨማሪ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እንሰራለን፡፡

ንጋት፡አካል ጉዳተኝነት በዓለምና በኢትዮጵያ ደረጃ ምን ይመስላል?

እጩ ዶክተር ሁሪያ አሊ፡  በአለም ላይ አካል ጉዳተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍል ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህም 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ይህ ቁጥር በአለም ላይ ካለው ከጠቅላላ ህዝብ 15 ነጥብ 3 ከመቶ የሚይዝ ሲሆን በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ላይ ከ15 እስከ 20 በመቶ እንደሚደርስም የአለም ባንክ መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ ባሉ የአፍሪካ አገሮች ላይ ጁን 2011 በተካሄደው ጥናት መሰረት በሀገራችን ከጠቅላላው ህዝብ 17 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆኑት ከተለያዩ አካል ጉዳቶች ጋር የሚኖሩ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው እስከ 18 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል፡፡

ንጋት፡በሀገራችን አካል ጉዳተኞችን የማሳተፍ ተግባር ምን ይመስላል?

እጩ ዶክተር ሁሪያ አሊ፡ በሀገራችን የወጡ በርካታ ህጎችና መመሪያዎች ቢኖሩም አሁንም ቢሆን ከአድሎና መገለል ነጻ መሆን አልቻሉም፡፡ ይህም ከትምህርት፣ ከስራ፣ ከመረጃ፣ ከመሰረታዊ ልማት፣ ከጤና አገልግሎት፣ ከልማት ፕሮግራሞች ከኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞች ከትራንስፖርት አገልግሎትና ሌሎች መሰል ጉዳዮችን ያጠቃልላል፡፡

 የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ የሁሉም ዜጋ ጉዳይ መሆኑን እያንዳንዱ ዜጋ ተገንዝቦት እኩል ተጠቃሚና ተሳታፊነት ማሳደግ ተገቢ ነው፡፡ ለዚህም መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡ እንደ ሀገር የአካል ጉዳተኞችን እኩል ተጠቃሚነትና ተሳታፊነትን ለማሳደግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን በዚህም የተለያዩ ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ወጥተው እና አለም አቀፍ ስምምነቶች ተፈርመው ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህም ስምምነቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካል ጉዳተኞች ኮንቬንሽን ነው፡፡

ይህ ስምምነት የሀገራችን የህግ አካል ሆኖ እየተተገበረ ሲሆን በሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን አስተባባሪነት የመንግስት አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች በሚወጡ ፖሊሲዎች፣ ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች እንዲሁም እቅዶች ውስጥ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ አካቶ እንዲሰሩ ያስገድዳል፡፡

የኮንቬንሽኑ ተጠቃሚነት ሲታይ እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም አሁንም የሚቀሩ በርካታ ስራዎች እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡

ንጋት፡በሀገራችን የአካል ጉዳተኞች ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?

እጩ ዶክተር ሁሪያ አሊ፡ ዜጎች በቤተሰብና በማህበራዊ ህይወት ውስጥ በንቃት መካተትና መሳተፍ ለሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ ነው፡፡ በማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የመሳተፍ እድሎችን ማግኘት በአንድ ሰው ስብእና ግንባታ፣ በኑሮ ሁኔታ እና በራስ መተማመን እንዲሁም በማህበራዊ ግንኙነት ላይ የሚያሳደረው አወንታዊ ፋይዳ የጎላ ነው፡፡

ከዚህ አንጻር አካል ጉዳተኞች የተለያዩ ማህበራዊ ተግዳሮቶችን ለመጋፈጥ ይገደዳሉ። ከማህበረሰብ አመለካከት እና ምላሽ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ አካል ጉዳተኞች በቤተሰብና በሌሎች ማህበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ለከፍተኛ ተግዳሮቶች የተጋለጠ ነው።

እንደ ተግዳሮት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል ህብረተሰቡ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ያለው አመለካከት የተዛባ መሆኑ አንዱ ነው፡፡ አሁንም መድሎና መገለል ይስተዋላል፡፡ ሴት አካል ጉዳተኞች በተደራራቢ ጫና ምክንያት ለችግር መጋለጣቸው፣ የህንጻ የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የትራንስፖርት የሚዲያ ተደራሽነት፣ የአካቶ ትምህርት ተደራሽነት እና የመሳሰሉት እንደ ተግዳሮት የሚነሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ከመስራት አኳያ ለውጦች ቢኖሩም በሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡ በአንድ ተቋም ወይም በተወሰኑ አካላት የሚሰሩ ስራዎች ብቻ አካል ጉዳተኞችን የእኩል እድል ተጠቃሚነትና ተሳታፊነትን በሚፈለገው መጠን ማሳደግ አይቻልም፡፡

ንጋት፡የአካል ጉዳተኞች ቀን መከበር ፋይዳው እንዴት ይለጻል?

እጩ ዶክተር ሁሪያ አሊ፡ የአለም የአካል ጉዳተኞች ቀን በሀገራችን ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ በየአመቱ በፌዴራል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትርና በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበር አስተባባሪነት ሲከበር ቆይቷል፡፡ የዘንድሮ የአካል ጉዳተኞች ቀንም “የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና በማጉላት አካታችና ዘላቂ ልማትን እናረጋግጣለን!”፥ በሚል መሪ ቃል በሀዋሳ ከተማ በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል፡፡

መሪ ቃሉ የአካል ጉዳተኞችን ተጽዕኖ ፈጣሪነት እና የመሪነት ሚና በህብረተሰቡ ውስጥ የማሳደግ አስፋላጊነት እና አካል ጉዳተኞች ውሳኔ ሰጪነት ሚናቸውን እንዲያድግ ንቅናቄ ለመፍጠር ነው፡፡

የዚህ በዓል ዋነኛው አላማ አካል ጉዳተኞች የእኩል እድል ተሳታፊና ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻልና በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለውን የተዛባ አመለካከት ለመቅረፍ ነው፡፡  በአጠቃላይ የበዓሉ መከበር አካል ጉዳተኞች በመንግስትና በህብረተሰቡ ዘንድ ትኩረት እንዲሰጣቸው ለመቀስቀስ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

ንጋት፡ስለሰጡኝ ማብራሪያ በድጋሚ አመሠግናለሁ፡፡

እጩ ዶክተር ሁሪያ አሊ፡ እኔም አመሠግናለሁ፡፡