የደረሱ ምርቶችን በወቅቱና በአግባቡ በመሰብሰብ የምርት ብክነት እንዳይከሰት በቅንጅት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 30/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደረሱ ምርቶችን በወቅቱና በአግባቡ በመሰብሰብ የምርት ብክነት እንዳይከሰት በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸውን በሀላባ ዞን የአቶቲ ኡሎ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ።

በወረዳው ከ21 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ አዝርዕት የተሸፈነ ሲሆን፥ 99 በመቶ የደረሱ ምርቶችን መሰብሰብ መቻሉን የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት አስታውቋል።

በዞኑ በአቶቲ ኡሎ ወረዳ አርሶ አደሩ የደረሱ ምርቶችን በመሰብሰብ ዘመቻ ላይ መሆናቸው ተመላክቷል።

የጤፍ፣ የበቆሎ፣ የዳጉሳ የድንችና ሌሎች የተለያዩ ምርቶችን በነቂስ ወጥተው እየሰበሰቡ መሆናቸውን በወረዳው ያነጋገርናቸው አንደንድ አርሶ አደሮች ተናግረዋል።

ምርት በጊዜ መሰብሰብ  የምርት ብክነት እንዳይከሰት ከማድረጉም በላይ ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለማትረፍ አስተዋፅኦ እንዳለው የጠቆሙት በወረዳው የደበሶ ቀበሌ ሞዴል አርሶ አደሮች አቶ ኢብሮ አማን እና ሱሊማን ሳሎ ናቸው።

የደረሱ ምርቶችን በወቅቱና በአግባቡ መሰብሰብ ካልተቻለ በቦታው የመራገፍ፣ ለተለያዩ በሽታዎች የመጋለጥና በከብቶች አደጋ ሊደርስበት እንደሚችል ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ተሞክሮ አስረድተዋል።

በሌላ በኩል የበቆሎ ምርታቸውን በወቅቱ እየሰበሰቡና በመፈልፈያ ማሽን እያስፈለፈሉ ያገኘናቸው አርሶ አደሮች በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ከነበረው አድካሚና ባህላዊ ከሆነ አሠራር ተላቀው በቴክኖሎጂ መታገዛቸው ግዜያቸውንና  ጉልበታቸውን  ከብክነት ከማዳን ባሻገር ከምርት ብክነት አንዳተረፋቸው ተናግረዋል።

በመሆኑም ወደ ሜካናይዜሽንና ግብርናን በቴክኖሎጂ አስደግፎ ምርታማነትን ለማጎልበት እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የጠቆሙት  አርሶ አደሮቹ ሁለንተናዊ ውጤቱ ከፍተኛ መሆኑን በመግለፅ ቴክኖሎጂው ይበልጥ ተስፋፍቶ በግብርናው ዘርፍ የሚገኘውን ውጤት ከፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል።

የባለሙያ ድጋፍና ክትትል እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ የሚሰጡት ትኩረት በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክት መሆኑን በመገንዘብ፥ ምርትና ምርታማነትን ይበልጥ እንዲሻሻል ሁሉም አካል በጋራ ሊሠራ ይገባል ስሉም ገልፀዋል።

የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ባለሙያ የሆኑት አቶ ሸምሱ ሪባቶ እንዳሉት የግብርና ሥራ የባለሙያ ቅንጅትን የሚሻ በመሆኑ በወረዳው ለሚገኙ አርሶ አደሮች አስፈላጊ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ምርትና ምርታማነት እንዲሻሻል ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የአቶቲ ኡሎ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ኃለፊ አቶ አህመዲን ሀላል በበኩላቸው በወረዳው እስከ አሁን ባለው ከ21 ሺ ሄክታር መሬት  በአጠቃለይ 99% ያህል ምርት መሰብሰቡን አስረድተዋል።

የደረሱ ምርቶች ለብክነትና ለሌሎች ተያያዥ ችግሮች እንዳይጋለጡ አርሶ አደሩ በወቅቱ ምርቱን ሰብስቦ ወደ ቀዬው እንዲወስድ በርካታ ቅንጅታዊ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ኃለፊው ገልጸው፥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለግብርናው ዘርፍ እየተሰጠ ያለው ትኩረት እያደገ በመምጣቱ በወረዳው ከዓመት እስከ ዓመት የምርት መጠን በአንፃሩ እያደገ ስለ መምጣቱም አንስተዋል።

ከቅርብ ጊዜ በኋላ የበርበሬ ምርት እንደ ዞን የሚሰበሰብ መሆኑን ተከትሎ በወረዳው አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ግብርናውን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የምርት መጠንን ይበልጥ ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉት ቅንጅታዊ ሥራዎች የሚበረታቱ  እንደሆነ የጠቆሙት አቶ አህመዲን የሚስተዋሉ የቴክኖሎጂ ግብዓትና ሌሎች ክፍተቶችን ለመቅረፍ ከአጎራባች ዞኖችና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

ዘጋቢ: አብዱልሰመድ አወል – ከሆሳዕና ጣቢያችን