የክልላዊ የፀረ ሙስና ቀን የማጠቃለያ ፕሮግራም እየተካሄደ ነው

ሀዋሳ፡ ሕዳር 27/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) “ወጣቶችን ያማከለ የፀረ ሙስና ትግል የነገን ስብዕና ይገነባል” በሚል ሚሪ ቃል ክልላዊ የፀረ ሙስና ቀን የማጠቃለያ ፕሮግራም በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነው።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉሰው ዘውዴ እንደገለፁት፥ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ21ኛ፣ በሀገራችን ለ20ኛና በክልሉ ለ3ኛ ጊዜ የሚከበረው የጸረ ሙስና ቀን “ወጣቶችን ያማከለ የፀረ ሙስና ትግል የነገን ስብዕና ይገነባል” በሚል መሪ ቃል መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በዓሉ በ2016 ዓ.ም ሙስና የጋራ ጠላታችን ነው በህብረት እንታገል በሚል መሪ ቃል በሁሉም ደረጃ ለ19ኛ ጊዜ እንደተከበረና በመርሃ ግብሩ 70 ሺህ 757 ሰዎችን በማሳተፍ ለፀረ ሙስና ትግሉ ያለውን ቁርጠኝነትን ማረጋገጥ መቻሉን ኮሚሽነሩ ገልፀዋል።

የበዓሉ መከበር ሙስናን በወሳኝ መልኩ ሊያርም የሚችልና የሀገሪቱ ባለቤት የሆነውን የወጣቱ ክፍል ባለቤት ማደረግን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ኮሚሽነር ሙሉሰው ተናገረዋል።

በሁሉም መልኩ ሙስናን ለመዋጋትና በህብረተሰቡ ውስጥ ታማኝነትን ለማጎልበት ያለውን የጋራ ኃላፊነት ለማጠናከርና በመሪ ቃሉ ወጣቶች ግልፀኝነትና ተጠያቂነትን የማስፈን ባህል ለማጎልበት እንደሆነ ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

ሙስና የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዘረፍ በትምህርት፣ በስራና በማህበራዊ እንቅስቃሴ ተፅዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ ሙስናን በብቃት መታገል ይገባል ብለዋል።

በተለይም የበዓሉ ታዳሚዎች የሀይማኖት መሪዎች የሀገር ሽማግሌዎች እና የሚዲያ ተቋማት ሙስና በህብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረውን ጫና በመረዳት የትውልድ ክፍተቶችን በመቅረፍ ሚናቸውን እንዲወጡ ኮሚሽነር ሙሉሰው ዘውዴ አስገንዘበዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አማካይነት እየተከበረ ያለው የፀረ ሙስና ቀን በዓል በተለያዩ ጭውውት ስነ ፅሑፍና በተማሪዎች የጥያቄና መልስ ውድድር እየተከበረ ነው።

ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን