የአካባቢያቸው የጸጥታ ሁኔታ መሻሻሎች በመታየቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ መጀመሩ እንዳስደሰታቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ
የአካባቢያቸው የጸጥታ ሁኔታ መሻሻሎች በመታየቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ መጀመሩ እንዳስደሰታቸው የቱም ማጂ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የመጣውን ሰላም ለማስቀጠል የሁሉም አካላት ድርሻ የጎላ ሊሆን እንደሚገባም የምዕራብ ኦሞ ዞን አስተዳደር አስታውቋል።
ከአዲስ አበባ በፊት በ1870 ዓ.ም በንጉስ ወልደጊዮርጊስ እንደተመሰረተች የሚነገርላት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በምዕራብ ኦሞ ዞን የምትገኘው የአሁኗ የቱም ማጂ ከተማ አስተዳደር ከ1870 ጀምሮ በከፋ ክፍለ ሀገር የማጂ አውራጃ በመሆን እንዲሁም በ1954 ደግሞ ከቀድሞ ንጉስ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የማዘጋጃ ቤት እውቅና አግኝታ የነበረች ከተማ እንደነበረች የታሪክ ማህደሮቿ ይጠቁማሉ።
በተለይም በአካባቢዋ ያለው የማእድን ሀብቶቿ፣ የእንስሳት ግብይት እና የሰብል ልማቶቿ በወቅቱ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የምታስተናግድ ከተማ የነበረች ሲሆን ከ1940 እስከ1994 የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላንም ተጠቃሚም ነበረች።
ይህቺ እረጅም እድሜ ያስቆጠረች ከተማ መንግስታት በተፈራረቁ ቁጥር እድገቷ በተፈለገው ልክ ሊጓዝ አለመቻሉን ነው የከተማዋ ነዋሪዎች የሚናገሩት።
በተለይም የመሰረተ ልማት አለመኖር አንዱ ሲሆን በአካባቢው ካሉ አጎራባች ህዝቦች ጋር በነበረው አለመግባባቶች በሚፈጠር የጸጥታ ችግሮች ለከተማዋ እድገት ማነቆ እንደነበር እና ለሰዎች ህይወት መጥፋትም መንስኤ መሆኑን ነው ነዋሪዎቿ የሚገልጹት።
ይህንን የጸጥታ ችግር በተለይም ጠቅላይ ሚኒስተሩ ለጉብኝት ወደ ከተማይቱ በመጡበት ወቅት ጸጥታውን ለማስተካከል እና ሰላም ለማምጣት ቃል ገብተው ከሄዱ በኋላ በተሰራው የጸጥታ ስራ ሰላም መስፈኑን ተናግረው ከጎረቤት ወረዳ ካሉ ህዝቦች ጋር ገበያ መገበያየት መጀመር መቻላቸውን ይናገራሉ።
ይህ ሁኔታም ዘላቂነት እንዲኖረው ህብረተሰቡም የበኩሉን እንደሚወጣም ጠቁመዋል።
በምዕራብ ኦሞ ዞን የቱም ማጂ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እሸቱ አየለ በበኩላቸው፤ ለከተማዋ እድገት አንዱ ማነቆ የሆነው የጸጥታ ችግር አሁን ላይ እየተፈታ በመምጣቱ የከተማዋን እንቅስቃሴ እያነቃቃው መሆኑን ይናገራሉ።
በተለይም አጎራባች ወረዳ የሚገኙ የሱርማ ብሔረሰቦች የጸጥታው ሁኔታ ከተስተካከለ በኋላ በጋራ ገበያ መገበያየት መጀመራቸው፣ ሰው ወደሚፈልገው አቅጣጫ በሰላም መንቀሳቀስ መቻሉ፣ የንግድ ስርአቱ መጠናከሩ ሰላሙ ያመጣው ለውጥ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ የመጣው ሰላም ወደ ኋላ እንዳይቀለበስ ህብረተሰቡም ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር በመሆን መጠበቅ አለበትም ብለዋል።
በተለይም በአርብቶ እና በከፊል የአርሶ አደር ወረዳዎች ይታይ የነበረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ ውጤት እየተገኘበት መምጣቱን የምዕራብ ኦሞ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ በድሉ መአዛ ተናግረዋል።
በተለይም የአካባቢውን ሰላም ለመመለስ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የክልሉ አድማ ብተና የክልሉ ፖሊስ ከአመራር አካላቱ ጋር ተቀናጅቶ በመስራታቸው ዛሬ ላይ በተለይም በሱርማ፣ ቤሮ እና ማጂ ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች ህዝቡ በሰላም ወጥቶ መግባት ከመጀመራቸውም ባለፈ ገበያ መገበያየት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
የህዝቡን ሰላም በማወክ በወጀል እጃቸው ያለባቸውን ተጠርጣሪዎች ወደህግ የማቅረቡ ስራ እየተሰራ ሲሆን ይህን ሰላም አስጠብቆ ከመሄድ አንጻርም ህብረተሰቡ የሰላሙ ዘብ መሆን ይገባዋልም ብለዋል።
ዘጋቢ: አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
ተቀራርቦ በጋራ መሥራት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያዝ ተጠቆመ
የጀፎረ ባህላዊ አውራ መንገድን ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ተጠቆመ
በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የማስተማር አቅም ግንባታ ለትምህርት ባለድርሻ አካላት ስልጠና ተሰጠ