የበጋ መስኖ ልማት ሥራ በተጠናከረ መልኩ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

የበጋ መስኖ ልማት ሥራ በተጠናከረ መልኩ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 26/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የበጋ መስኖ ልማት ሥራ በተጠናከረ መልኩ እየተሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጠምበሮ የልዩ ወረዳ ግብርና ልማት ጽ/ቤት አስታወቀ።

በልዩ ወረዳው በ2017 ምርት ዘመን 3 ሺህ 422 ሄክታር ማሳ ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱ ተጠቁሟል።

የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት የእርሻ  ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተመስገን በርገኖ እንደገለጹት በልዩ ወረዳው በ2017 ምርት ዘመን የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም 3 ሺህ 422 ሄክታር ማሳ ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አስታውሰዋል።

አቶ ተመስገን አክለውም በ1ኛ ዙር በጓሮ አትክልትና በስራስር ሰብሎች 596 ሄክታር ማሳ ማልማት መቻሉንም ጠቅሰዋል።

ቀሪ ሥራዎችን ለማሳካት ግምባር ቀደም አርሶ አደሮችን፣ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ አርሶ አደሮችን በማደራጀት የተግባር ሥልጠና መስጠት መቻሉንም ጠቁመዋል ።

ለአርሶ አደሮቹ  በመደብ አዘገጃጀት፣ የጓሮ አትክልት አዘራር፣ የሰብሎች የዉሃ አሰጣጥና የሰብል እንክብካቤ እንድሁም የበሽታና የተባይ ቁጥጥር ጭምር ግንዛቤ መፈጠሩን አቶ ተመስገን ተናግረዋል።

የበጋ ስንዴን ጨምሮ ባሉን ጊዜያት ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፥ ለመስኖ ልማት አመቺ የሆኑ ቀበሌያትን በመለየት  የዘርፉ ባለሙያዎች ተመድበው በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ያስረዱት አቶ ተመስገን፥ ውጤቱን ለማሳካት  ክትትል እንደሚደረግም አስገንዝበዋል።

ያነጋገርናቸው የዘርፉ ባለሙያዎችም በበጋ መስኖ ልማት  ዉጤታማ ተግባራት መከናወኑን ገልጸው፥  ከዚህ በፊት በህብረተሰቡ ዘንድ ብዙም ትኩረት ያልነበረ ቢሆንም በአሁን ጊዜ የሚሰጠዉን ስልጠና ተገንዝበው የመስኖ ልማት ሥራ ተጠቃሚ ለመሆን ፍላጎት እንዳላቸዉ ተናግረዋል ።

በልዩ ወረደ ካነጋገርናቸው ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች መካከል ወይዘሮ አስቴር ሀይሌ እንዳሉት  ከዘርፉ ባለሙያዎች ባገኙት ስልጠና በመታገዝ  በመስኖ ልማት ተጠቀሚ መሆናቸውን  ተናግረዋል።

በቀን ሦሥት ዙር ከመብላት አልፈው ወደ ገበያ በማዉጣት ገቢ በማግኘት የተሻለ ኑሮ እንደሚኖሩም አርሶ አደሯ ገልጸዋል ።

አርሶ አደር ማርቆስ ኤሎ በበኩላቸዉ  የመስኖ ልማት ሥራን በባህላዊና ዘመናዊ  ዘዴ እያለሙ ረሃብን በማጥፋት የተሻለ ኑሮ እየኖሩ እንደሆነ ገልጸዋል ።

በቀጣይ ከዚህም የበለጠ ለዉጥ ለማምጣት እንደሚሰሩ ጠቅሰዉ ከዚህ በፊት በበሬ እያረሱ ለዉጥ ያመጡትን ተሞክሮ ተጠቅመው በቀጣይ በትራክተር እያረሱ የተሻለ ምርት ለማምረት ፍላጎት እንዳለቸውም ተናግረዋል ።

ዘጋቢ፡ ማቴዎስ ሀደሮ – ከሆሳዕና ጣቢያችን