ፆታን መሰረት አድርጎ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመከላከል በየደረጃው የሚገኙ አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሴቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አሳሰበ

ፆታን መሰረት አድርጎ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመከላከል በየደረጃው የሚገኙ አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሴቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አሳሰበ

የነጭ ሪቫን ቀን “የሴቷ ጥቃት የእኔም ነው ዝም አልልም” በሚል መሪ ቃል ከአክሽን ኤይድ ኢትዮጵያ ሚዛን አማን ቅርንጫፍ ጋር በመተባበር በቦንጋ ከተማ ተከብሯል።

የቢሮው ሀላፊ ወ/ሮ ገነት መኩሪያ፤ ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት በሴቶች ላይ የሚፈፀም ማንኛውም ዓይነት አካላዊ፣ ወሲባዊ፣ ሰነ ልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር የሚያስከትል የሰብአዊ መብት ጥሰት ነዉ ብለዋል።

በሴቷ ላይ የሚደርሱ ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከልና ለማስወገድ በመንግስት የተያዙ ዕቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ ህብረተሰቡን በማነቃቃት ጥቃትን ባለመታገሰ ፆታዊ ጥቃት እንዲቀንስ ብሎም እንዲወገድ መስራት ይገባል ብለዋል።

የቢሮው ምክትል ሀላፊ ወ/ሪት ለምለም አምሳሉ፤ ቀኑን አስመልክቶ ባቀረቡት ሰነድ ላይ በመድረኩ ተሳታፊዎች ምክክርና ዉይይት ተደርጎበታል።

በመድረኩ ከተገኙት መካከል የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቆጭቶ ገ/ማርያም እና የክልሉ ፍትህ ቢሮ ሀላፊ አቶ እሼቱ ጎዴቶ፤ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።

ተሳታፊዎቹ አክለውም ሴቷ ጥቃት ደረሶባት ወደ ፍትህ ስትቀርብ የነፃ ህግ አገልግሎት ከመስጠትና ከሀብት ክፍፍል ጋር እኩል ተጠቃሚ እንድትሆን መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ በክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቆጭቶ ገ/ማርያም አማካኝነት፤ በሴቶች እና ህፃናት ላይ ማንኛውም ዓይነት ጥቃት እንዳይፈጸምና ተፈጽሞ ሲገኝ ዝም ላለማለት በተሳታፊዎች ቃል ተገብቷል።

ዘጋቢ፡ በረከት ታደሰ – ከቦንጋ ጣቢያችን