ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ፣ የአካል ጉዳት እና ኢኮኖሚያዊ የአቅም ውስንነት ያለባቸው ዜጎችን ለማገዝ በሚደረገው ጥረት የሁሉም ባለድርሻ አካል ቅንጅታዊ ስራ ሊሆን እንደሚገባ ተገለፀ
ይህ የተገለጸው በቀቤና ልዩ ወረዳ በመንግስትና በበጎ አገልግሎት ማህበራት የተከናወኑ የ2016 የክረምት በጎ ፈቃድ ስራዎች አፈፃፀም እና የ2017 የበጋ በጎ ፈቃድ አግልግሎት ማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ በተካሄደበት ወቅት ነው።
የልዩ ወረዳው ወጣቶች እና ስፖርት ጽ/ቤት ከማህበራዊ እና ሰራተኛ ጽ/ቤት ጋር በጋራ ባዘጋጁት መድረክ ላይ የተገኙት የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ እንደገለፁት፤ በ2016 የክረምት በጎ ፈቃድ ስራ በርካታ ጠዋሪና ደጋፊ የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ማገዝ የተቻለ ሲሆን 27 መኖሪያ ቤቶች በመገንባት ድጋፍ ለሚሹ አቅመ ደካሞች ማስረከብ ተችሏል።
በአጭር ጊዜ በተሰራው የበጎ አገልግሎት ተግባር ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን እንደተቻለ የገለፁት አስተዳዳሪው ከተጋገዝን ከዚህም በላይ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ተናግረዋል።
የስፖርቱን ዘርፍ በማጠናከር ረገድ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች በመጠበቅና ፕሮጀክቶችን በመደገፍ በዘርፉ የሚጠበቀው ውጤት ለማምጣት ከቀበሌ ጀምሮ በቅንጅት መስራት ይጠበቃል ብለዋል።
የቀቤና ልዩ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ጁዋር ጀማል በበኩላቸው፤ በሀገር ደረጃ የተጀመረው የክረምት በጎ ፈቃድ ስራ እንደ ልዩ ወረዳ በሁሉም ዘርፍ ማህበረሰቡን የወጣት አደረጃጀት እና አመራሩን በማስተባበር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ አረጋውያንና እንዲሁም ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን በቤት ግንባታ፣ በደም ልገሳ፣ በትምህርት ቁሳቁስና አልባሳት መደገፍ ተችሏል ነው ያሉት።
የተመዘገቡ አዎንታዊ ውጤቶችን በማስቀጠልና ድክመቶችን በማረም መስራት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ጁዋር ቀበሌዎች አካባቢ ከወጣት ስፖርታዊ ማዘውተሪያ ስፍራዎች ጥበቃ ማነስ እና የስፖርቱ ዘርፍ ድጋፍ አንፃር በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
የቀቤና ልዩ ወረዳ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ደምስ በስር፤ በ2016 የክረምት በጎ ፈቃድ ስራዎች ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ ዜጎችን ለመደገፍ በተደረገው ጥረት እንደ ልዩ ወረዳ አንድም ተረጂ መኖር የለበትም በሚል ማህበረሰቡና እና ወጣቶች በማሳተፍ በክልል ደረጃ እውቅና የተሰጠው ስራ መሰራቱን ገልፀዋል።
በቀጣይ በተጀመረው የ2017 የበጋ በጎ ፈቃድ ተግባራት ከቀበሌ ጀምሮ ደጋፊና ጠዋሪ አጥተው ለችግር የተጋለጡ ዜጎች ልየታ በማድረግ የተሻለ ስራ መሰራት እንዳለበት ተናግርዋል።
ከበመድረኩ ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት መካከል አቶ ሲራጅ ሀጂ ዱላ በሰጡት አስተያየት፤ እንደ ልዩ ወረዳ በ2016 የክረምት በጎ ፈቃድ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙና ደጋፊ የሌላቸው ወገኖች በማገዝ የተሰራው ስራ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ አዱኛ ትዕዛዙ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
ተቀራርቦ በጋራ መሥራት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያዝ ተጠቆመ
የጀፎረ ባህላዊ አውራ መንገድን ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ተጠቆመ
በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የማስተማር አቅም ግንባታ ለትምህርት ባለድርሻ አካላት ስልጠና ተሰጠ