የቡናን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያረጁና ምርት የማይሰጡ ቡናዎችን በአዲስ ለመተካት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

የቡናን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያረጁና ምርት የማይሰጡ ቡናዎችን በአዲስ ለመተካት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

የቡናን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያረጁና ምርት የማይሰጡ ቡናዎችን በአዲስ ለመተካት እየሠራ መሆኑን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ ግብርና ልማት ጽ/ቤት አስታውቋል።

በወረዳው የ2017 ምርት ዘመን የቡና ዕደሳ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ተካሂዷል።

በማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ ንግግር ያደረጉት የጌዴኦ ዞን ምክትል አስተዳደሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ ታጠቅ ዶሪ በበኩላቸው፤ በእርጅና ምክንያት ምርት የማይሰጠውን የቡና ዛፍ በአዲስ ለመተካት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ ከቡና ባሻገር በሌሎች ሥራዎች ተሳታፊ እንዲሆን በማድረግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንቅስቃሴ መጀመሩን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ ሚጁ እንደገለፁት፤ ቡናን በኩታ ገጠም ማምረት በጀመሩ አጎራባች ወረዳዎች ከአርሶ አደሩና የግብርና ባለሙያዎች ጋር የመስክ ምልከታ በማድረግ በወረዳው በዓመቱ ከ46 ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም ለማልማት አቅደው ወደ ተግባር ገብተዋል፡፡

የቡናን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያረጁና ምርት የማይሰጡ ቡናዎችን ሙሉ በሙሉ በማደስ በአዲስ ለመተካት እየሠሩ መሆናቸውን የተናገሩት የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ክፍሌ ጂግሦ የተቀናጀ የግብርና ልማት አሠራርን በመከተል ቡና እስኪደርስ ተመጋጋቢ የሆኑ ሰብሎችን እንዲያመርቱና በእንስሳት እርባታ አርሶ አደሩን ለማሳተፍ መታቀዱን ጠቅሰዋል፡፡

በመስክ ምልከታው ባገኙት ግንዛቤ ዓመታትን ያስቆጠሩ የቡና ዛፎችን በአዲስ ለመተካት መዘጋጀታቸውን ከወረዳው አርሶ አደሮች መካከል ዳዊት ግዛው እና ፀጋዬ ዶሪ በሰጡት አስተያየት አስረድተዋል።

ዘገቢ፡ ውብሸት ኃይለማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን