በቡርጂ ዞን ሶያማ ከተማ አስተዳደር የከተማ አቀፍ የአካባቢ ልማትን የሚያሳልጥ የህብረተሰብ ተሳትፎ አደረጃጀት ተመሰረተ
በተመሠረቱት አደረጃጀቶች ውስጥ የተመረጡት የኮሚቴ አባላትም ሥራቸውን በአግባቡ ለመሥራት ቃል ገብተዋል።
የምስረታ መርሃ-ግብሩን የመሩት የሶያማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ፍስሃ አድማሱ በበኩላቸው፤ ሶያማ ከተማን ለማልማት መንግስትና ነዋሪው ህዝብ እጅ ለእጅ ተያይዞ እንዲጓዝ የልማት አደረጃጀት ማዋቀር አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የሶያማ ከተማን ለማልማት እኛ ካልተጋን ሌላ አካል መጥቶ አያለማልንም ያሉት ከንቲባው፤ ባለን አቅም ሁሉ ለልማታዊ ሥራ ልንረባረብ ይገባናል ሲሉም አሳስበዋል።
ለከተማ ልማት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተሳታፊ መሆን እንዳለበት ተናግረው የሶያማ ከተማን ለማልማት የተመረጡ ኮሚቴዎች ኃላፊነታቸውንና ተግባራቸውን በብቃት እንደሚወጡ ተስፋ እንደተጣለባቸዉ የሶያማ ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ማሞ ዋሬ ገልጸዋል።
የተመሰረቱ አደረጃጀቶች አብይ እና ንኡስ ኮሚቴዎች ሥር የቅስቀሳ፣ የፋይናንስ እና የኦዲት ኮሚቴዎች ተመርጠዋል።
የተመረጡ የአብይ እና ንኡስ ኮሚቴዎችን ጨምሮ ሌሎች ኮሚቴዎች ኃላፊነት እና ተግባር በዝርዝር የቀረበ ሲሆን የሚሠሩ ተግባራትን ማቀድ፣ መፈፀም፣ ቅስቀሳ እና ግንዛቤ መፍጠር፣ የተሠሩ ሥራዎችን መገምገም፣ በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ለህዝቡ መረጃ መስጠት፣ ሀብት ማሰብሰብና መሰል ተግባራት መሆናቸውም በመድረኩ ተመላክተዋል።
የልማት የኮሚቴ አባላት በሕብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው፣ ሠርተው ማሠራት የሚችሉ እና ለልማቱ ቁርጠኞች መሆናቸውንም በተሳታፊዎች አስተያየት የተሰጠ ሲሆን ኃላፊነታቸውን በተጠያቂነት መንፈስ በአግባቡ ለመሥራትና የህዝብን አደራ ለመወጣት ቃል ገብተዋል።
ዘጋቢ፡ ወርቅአገኘሁ ወልደየስ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው – የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/