የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሌሎች የመሠረተ ልማት ስራዎችን ከህብረተሰቡ ጋር እየሠራ መሆኑን የኮሬ ዞን ኬሌ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ
በአገልጋይነት ስሜት በጋራ መስራት ከቻልን የከተማው ዕድገት እሩቅ አይሆንም ብሏል ከተማ አስተዳደሩ።
በኮሬ ዞን የኬሌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ዮሐንስ ሐይሉ እንደተናገሩት፤ የከተማው አደባባይ ግንባታን ጨምሮ ሌሎች በተሠሩ የልማት ስራዎች ሕብረተሰቡ በገንዘቡ፣ በእውቀቱና በጉልበቱ ተሳትፏል።
በዚህም ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ የተገመተውን የአደባባይ ግንባታ 4 ሚሊዮን ብር ባልሞላ ማጠናቀቅ መቻሉን አመላክተው፤ ሌሎች የልማት ስራዎችም ከህብረተሰቡ ጋር እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አሁን ላይ እስከ 1 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት፣ 4 ኪሎ ሜትር የመንገድ መብራትና እስከ 1.5 ኪሎ ሜትር የሚሆን የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ከፈታ በህብረተሰብ ተሳትፎ ለማከናወን ድጋፍ መጀመሩን ከንቲባው ተናግረዋል።
ለዚህ ሥራ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ያስፈልገናል ያሉት ከንቲባው፤ ሁሉም ለኬሌ ከተማ ዕድገትና ልማት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የህብረተሰብ ተሳትፎ አስተባባሪ የሆኑት አቶ አስፋው አሸናፊ በበኩላቸው፤ የኮሬ ህዝብ ድጋፉን አጠናክሮ በመቀጠል የራሱን አሻራ ማሳረፍ አለበት ብለዋል።
ወ/ሪት ደሳለች ዳኜ እና አቶ ረዳሄኝ ኩንታ ለሚሰሩ የልማት ሥራዎች ድጋፍ ካደረጉት የህበረተሰብ ክፍሎች መካከል ሲሆኑ የኬሌ ከተማ የሚፈለገውን ያህል ዕድገትና ለውጥ ሳታሳይ እንደቆየች አስታውሰው፤ ከበፊቱ ይልቅ አሁን ላይ በአይን የሚታዩ የልማት እንቅሰቃሴዎች እንዳሉ ነው የገለጹት።
ለከተማችን ዕድገትና ውበት አሻራችንን በማኖራችን ዕድለኞች ነን የሚሉት ነዋሪዎቹ፤ በአንድነት በመስራት ለውጥ ማምጣት እንችላለን ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡ ለምለም ኦርሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
አካል ጉዳተኞች መብቶቻቸውና ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ በቅንጅትና በጥምረት መስራት እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለፀ
አካባቢን በመጠበቅና በማጽዳት ምቹና ጽዱ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ሁሉም የድርሻውን ልወጣ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አሳሰቡ
ግለሰባዊ ነጠላ ትርክቶችን በጋራ በመታገል በመደመር እሳቤ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተገለጸ