የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ማዕከል ከአለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በክልሉ ከምባታ ዞን ዶዮገና ወረዳ የጀመረው የትሮፒካል የዶሮ ዝርያ ማሻሻያ ፕሮጀክት ውጤታማ እንዳደረጋቸው በፕሮጀክቱ የታቀፉ አርሶ አደሮች ተናገሩ

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ማዕከል ከአለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በክልሉ ከምባታ ዞን ዶዮገና ወረዳ የጀመረው የትሮፒካል የዶሮ ዝርያ ማሻሻያ ፕሮጀክት ውጤታማ እንዳደረጋቸው በፕሮጀክቱ የታቀፉ አርሶ አደሮች ተናገሩ

ማዕከሉ የፕሮጀክቱ የቆይታ ጊዜ መገባደዱን ተከትሎ በወረዳው አመቾ 01፣ አመቾ ዋቶና ወንጀላ አካባቢዎች በ2015 ዓ.ም በእንቁላል ጣይና ጥምር ጠቀሜታ ባላቸው የዶሮ ዝርያዎች የጀመረውን ስራ ውጤታማነት እየገመገመ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የእንስሳት ምርታማነትን ለማሻሻል በትብብር ከሚሰሩ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው የትሮፒካል የዶሮ ዝርያዎች ሶሉሽን-አካታች የእንስሳት ምርታማነት ማሻሻያ ፕሮጀክት (TPGS-SAPLING) ከክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በከምባታ ዞን ዶዮገና ወረዳ ከሁለት አመት በፊት ወደስራ  መግባቱ ተገልጿል።

አቶ ብርሃኑ ክበሞ እና ወ/ሮ ደመቀች ወ/ማሪያም በአመቾ ዋቶ እና አመቾ 01 አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ሲሆኑ “ቮቫን ብራውን” እና “ኮኮክ” የተባሉ የዶሮ ዝርያዎችን ከፕሮጀክቱ አግኝተው ውጤታማ እንዳደረጋቸው  ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል አርሶ አደር አለማየሁ ተሰማ፣ የሰይፉ ወልዴ እና ሰላሙ ያዕቆብ ከፕሮጀክቱ በኩል ያገኙትን እንቁላል ጣይና ጥምር ጠቀሜታ ያላቸውን ዶሮዎችን በማርባት የምግብ ፍጆታቸውን ከማረጋገጥ አንስቶ ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያቸውን መደጎም እንደቻሉም ነው ያስታወቁት።

በአመቾ ዋቶ እና አመቾ 01 አካባቢ የእስሳት እርባታ ባለሙያዎች የሆኑት አስናቀች ቀልቦሬ እና ብርሃኑ ጡሜቦ ለአርሶ አደሮቹ የግንዛቤ ስራ ከመስራት ጀምሮ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ በማድረጋቸው የታየው ለውጥ አበረታች እንደሆነ አንስተዋል።

በምርምር ኢንስቲትዩት ማዕከሉ የእንስሳት ምርምር ደይሬክተር ዶክተር ደርቤ ገሚዩ እንደገለጹት፤ በወረዳው አመቾ 01፣ አመቾ ዋቶ እና ወንጀለ ቀበሌያት በ2015 ዓ.ም ተግባራዊ የተደረገው የእንቁላል ጣይና ጥምር ጠቀሜታ ያላቸው የተሻሻለው የዶሮ ዝርያ የውጤታማነት ደረጃ እየተገመገመ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በዋናነት በዶሮ መኖና በግብዓት አቅርቦት፣ በውጤታማነት ክትትል፣ በገበያ ትስስርና ተያያዥ ጉዳዮች ትኩረት በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃምነት ማረጋገጥ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ለዚህም እንዲያግዝ ከግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ጀምሮ የልምድ ልውውጥ ስራ መሰራቱን አስታውሰዋል።

የአርሶአደሩን የማርባት አቅምና ዝግጅት መሠረት ባደረገ መልኩ 25፣ 50 እና 75 በዝሪያ መጠሪያቸው “ቮቫን ብራውን”፣ “ሳሶ” እና “ኮኮክ” የተባሉ የዶሮ ዝሪያዎችን ለአርሶአደሩ ማቅረብ መቻሉን የተናገሩት ዶክተር ደሪቤ፤ የእያንዳንዳቸውን ዝሪያ የአዋጭነት መጠናቸው ጥናት ተደርጎ ወደ መረጃ ቋት እንደገባም አንስተዋል።

በተለይ ቮቫን ብራውን የተሰኛው የዶሮ ዝሪያ እንቁላል ጣይ ሲሆን ሳሶ እና ኮኮክ ጥምር ጠቀሜታ ያላቸው እንደሆነም ነው የጠቆሙት።

የክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የአየር ጠባይ ለዶሮ እርባታ አመቺ መሆኑን ያመላከቱት ዳይሬክተሩ፤ ነገር ግን በቆላማ፣ ደጋና ወይናደጋ የአየር ንብረት ባለባቸው አካባቢዎች እንደየአየር ሁኔታ  የተለያየ የአያያዝ ጥንቃቄን የሚጠይቅ እንደሆነ አስረድተዋል።

የተሻሻለውን የዶሮ ዝሪያን ማስፋፋት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር የስራ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮቹም ሆኑ ኢንተርፕራይዞች በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዘጋቢ: አለቃል ደስታ – ከሆሳዕና ጣቢያችን