በአብርሃም ማጋ
ከላይ በርዕሱ የገለጽነውን ሃሳብ ያነሳው የዛሬው ባለታሪካችን ነው፡፡ በመምህርነት እና በጋዜጠኝነት ሙያ ለረጅም ዓመታት አገልግሏል፡፡ የርዕሱን ሃሳብ ያነሳልንም በተሰማራባቸው እነዚሁ ሙያዎች በቆየባቸው ጊዜያት ካሳለፋቸው ልምድ በመነሳት ነው፡፡
በየትኛውም የሥራ መስክ ላይ ኩርፊያና ንትርክ ውጤታማነትን ያሽመደምዳል ሲልም ሃሳቡን ያጠናክራል፡፡ አኩራፊነት ካለ በመወያየት መግባባት እንደማይቻልም ይገልጻል፡፡
ሌላው ቀርቶ ኩርፊያና ንትርክ ውስጥ የገቡ ባለትዳሮች የተሻለ ህይወት ለመኖር ይቸገራሉ በማለት አክሏል፡፡ ካለመግባባታቸው የተነሳ ውጤታማም አይሆኑም፡፡ በዚህም ዞሮ ዞሮ እዳው ከእነሱ አልፎ ለልጆታቸው ይተርፋል ባይ ነው፡፡
ጋዜጠኛ ገናናው ይህንን በወጣትነቱ ተረድቶ በመምህርነትና በጋዜጠኝነት ለረጅም ዓመታት በሠራባቸው ጊዜያት ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ተግባብቶና ተስማምቶ የመሥራት ባህልን አዳብሯል፡፡
ጋዜጠኛ ገናናው ለማ በቀድሞው አስተዳደራዊ መዋቅር በጋሞ ጐፋ ጠቅላይ ግዛት በጋሞ አውራጃ፣ ጨንቻ ዙሪያ ወረዳ በጨንቻ ከተማ በ1957 ዓ.ም ነው የተወለደው፡፡ እድሜው ለትምህርት ሲደርስ በደጃዝማች ወልደማሪያም ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ተምሯል፡፡ በመቀጠልም ከ8ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተምሮ አጠናቋል፡፡
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና /ማትሪክ/ ሲወስድ ለዲፕሎማ የሚያበቃ ውጤት ማምጣት ቻለ፡፡ በዚህም ምክንያት በ1974 ዓ.ም ኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ገብቶ ለሁለት ዓመታት ትምህርቱን በመከታተል በ1975 ዓ.ም በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት በዲፕሎማ ተመርቋል፡፡
ከዚያም ሐምሌ 11/1975 ዓ.ም በአርሲ ክፍለ ሃገር ጭላሎ አውራጃ በሥሬ ከተማ ሥሬ ሁለተኛ ከፍተኛ ደረጃ ት/ቤት በእንግሊዝኛ ቋንቋ በመምህርነት ተቀጠረ፡፡
በትምህርት ቤቱም ለ5 ዓመታት በቋንቋ መምህርነት አገልግሏል፡፡ በ1980 ዓ.ም ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዲፕሎማ ትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ያላቸውን መምህራን አወዳድሮ በክረምት መርሃ ግብር በዲግሪ ፕሮግራም ለማስተማር ባወጣው መስፈርት መሠረት ተወዳድሮ በማለፍ በውጭ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሁፍ ለ7 ክረምቶች ተከታትሎ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል፡፡
ከነሐሴ 1/1980 ዓ.ም እስከ የካቲት 30/ 1984 ዓ.ም ድረስ ወደ አርሲ ነገሌ ከተማ ተዛውሮ በቋንቋ መምህርነት አስተምሯል፡፡
ከዚያም 1984 ዓ.ም ወደ ሃላባ አጠቃላይ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተዛውሮ እስከ 1996 ዓ.ም ድረስ ለ12 ዓመታት በቋንቋ መምህርነት አገልግሏል፡፡
በአጠቃላይ በመምህርነት ለ21 ዓመታት ያህል ሲያገለግል አንድ ዓመት በዩኒት መሪነትና በአብዛኛው በዲፓርትመንት ሃላፊነት ሰርቷል፡፡
ሃላባ በነበረበት ጊዜ ከመደበኛ ሥራው በተጨማሪ ሠርተፊኬት የነበራቸውን መምህራን ወደ ዲፕሎማ ደረጃ ለማሳደግ በርቀት ትምህርት እንዲከታተሉ የሚሰጣቸውን ሞጅሎችን በማጠንከሪያ ትምህርት ያስተምርም ነበር፡፡
ከዚህ ውጭም የእንግሊዝ መንግስት ከብሪትሽ ካውንስል ጋር በመተባበር አንድ ፕሮግራም ያዘጋጃል፡፡ ፕሮግራሙም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቃትን (English Proficency) ማሳደግ ነበር። በመሆኑም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቃት ላላቸው መምህራን የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቶ ከፍተኛ ብቃት ያላቸውን በፈተና አወዳድሮ የተወሰኑትን ይቀበል ነበር፡፡
ጋዜጠኛ ገናናውም ጥሩ የእንግሊዝኛ ብቃት ስለነበረው ፈተናውን አልፎ የምደባ ደብዳቤ ተሰጥቶት ዱራሜ ከተማ ደረሰው። በከተማዋም በሁሉም ትምህርት ደረጃ የሚገኙ መምህራን ጥሩ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ እንዲኖራቸው ለማድረግ ለበርካታ ዓመታት አሰልጥኗል፡፡
ጋዜጠኛ ገናናው ለማ ለ21 ዓመታት በመምህርነት ሥራ ተሠማርቶ በፈፀመው ተግባር በርካታ ለስኬት የበቁ ዜጎችን ማፍራት መቻሉን ሳይገልፅ አላለፈም፡፡ በአርሲ ነገሌ ከተማ ካስተማራቸው ተማሪዎች መካከል ሁለት ተማሪዎች በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀው በሃላባ አጠቃላይ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተመድበው አብረውት አስተምረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በባልደረባነት አብሮት የሚሰራ አንድ ጋዜጠኛም የእርሱ ተማሪ እንደሆነ ይናገራል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ዛሬ ላይ በሚኒስትር ደረጃ ሀገሪቱን እያገለገሉ የሚገኙም አልጠፉም።ቀደም በኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የነብሩ ዶክተር ያኒያ ሰይድመኬ ይነሳሉ፡፡
ጋዜጠኛው ከ21 ዓመታት የመምህርነት ቆይታ በኋላ ሙያውን ቀይሮ በ1996 ዓ.ም ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ ገብቷል፡፡
በወቅቱ የደቡብ ንጋት ጋዜጣ ከፍተኛ የሰው እጥረት ስለነበረበት በዝውውር ወደ ቀድሞ ደቡብ ክልል ባህልና ማስታወቂያ ቢሮ ተዛውሯል። እንደተዛወረም በደቡብ ንጋት ጋዜጣ ክፍል በረዳት አዘጋጅነት ተመደበ። በወቅቱ በ16 ገፆች የሚታተመውን ጋዜጣ ለሁለት ብቻ ሆነው ይሠሩ ነበር፡፡
እነዚህን ገፆች ለመሸፈን በሁለት ሰዎች ብቻ የሚደረግ እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ በወረዳዎች ደረጃ በማስታወቂያ ጽ/ቤቶች የነበሩ ሠራተኞች ጽሑፎችን እያዘጋጁ እንዲልኩላቸው መጋበዙ ግድ ሆነባቸው፡፡
በተጠቀሰው መልክ በጣም ከባድና አስጨናቂ የሆነውን ሥራ በከፍተኛ ትጋትና ጥረት እየሠራ ከቆየ በኋላ በቢሮው ውስጥ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት የሚባል መዋቅር ይዘረጋል፡፡ መዋቅሩም የሬዲዮ፣ የቴሌቪዥንና የጋዜጣ ክፍሎች ተብሎ ነበር የተዘረጋው፡፡
ቀደም ሲል የጋዜጣ ክፍል ዋና አዘጋጅ የነበረው የቴሌቪዥን ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሲመደብ፣ ጋዜጠኛ ገናናው የጋዜጣ ክፍል ዋና አዘጋጅ ሆነ። ሥራውን ለብቻው መሥራት የማይችለው ጉዳይ በመሆኑ ሌሎች አዘጋጆችን መመደብ የግድ ነበር፡፡
በዚሁም በወረዳዎች ሆነው ጽሑፍ አዘጋጅተው ከሚልኩላቸው ተሳታፊዎች ውስጥ ሁለቱን መርጦ በዝውውር እንዲመጡ ማድረግ ሌላው አማራጭ ነበር፡፡
እነዚህን ሁለቱን ሰዎች በዓይን አይቷቸው የማያውቃቸው ቢሆንም በሚጽፉት ጽሑፍ በብቃታቸው ብቻ አወዳድሮ በመመልመል ለቢሮ ኃላፊው ስማቸውን ጽፎ ያስተላልፋል።
እነዚህ አዘጋጆች በኃላፊው ፊርማ በዝውውር ወደ ሐዋሣ እንዲመጡ አስደረገ። በተጨማሪም አንድ ሰው ከመስሪያ ቤቱ እንዲመደብለት በጠየቀው መሰረት አንድ አዘጋጅ ተመደበለት፡፡ እነዚህን አዳዲስ የሰው ኃይል ይዞ ለ4 ሆነው 16 ገጾች ያሉትን ጋዜጣ በ15 ቀን አንዴ በማሳተም ቀልጣፋና ውጤታማ ሥራ እየሠሩ ቆዩ፡፡
እሱም በዋና አዘጋጅነት ለ6 ዓመታት በሠራባቸው ጊዜያት ጽሑፍ በማዘጋጀት፣ በአርትኦትና ርዕሰ አንቀጽ በመጻፍ ኃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡ በተጨማሪም በሠራተኞቹ መካከል ጥሩ የሥራ ድባብ በመፍጠር፣ በማግባባት እና በማስተባበር ሥራውን መርቷል፡፡
ከዚያም ከጋዜጣ ክፍል ወደ ዜና ክፍል ተዛውሮ በአርታኢነት ለሁለት ዓመታት ሠርቷል፡፡ በመቀጠልም በሬዲዮ ክፍል በከፍተኛ አርታኢነት ለረጅም ጊዜያት አገልግሏል፡፡ በሬዲዮ ላይ እየሰራ ሳለ አዲስ የአሰራር ለውጥ (ሪፎርም) ተጀምሮ በለውጡም በአርታኢነት ለአንድ ዓመት ያህል ሠርቷል፡፡
ከዚህ ውጭም እንደገና በጋዜጣ ዝግጅትና ስርጭት ክፍል በከፍተኛ አዘጋጅነት ለአንድ ዓመት ከሠራ በኋላ በአሁኑ ወቅት በድረገጽና ማህበራዊ ሚዲያ ክፍል በአርታኢነት ተመድቦ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ለዚህ ሥራ ክፍል ሊመደብ የቻለው የተለያዩ ሙያዊና መሰል ስልጠናዎችን በመወሰዱ ነው፡፡
ጋዜጠኛው በአሁኑ ወቅት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ክልላዊ የሆኑትን ዜናዎችን፣ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን፣ ስፖርታዊ ኩነቶችንና ሥነ ጽሑፋዊ ይዘት ያላቸውን የተለያዩ ጽሑፎችን በመለየት ማሰራጨት ይጠቀሳሉ፡፡ ሥራው በቀጥታ ስርጭት በድረ ገጽ፣ በፌስቡክ፣ በዩቲዩብ፣ በቴሌግራም፣ በትዊተር እና አጠቃላይ በበይነመረብ መረጃዎችን ማስተላለፍን ያጠቃልላል፡፡ መሠረታዊ የኮምፒዩተርና የፎቶ ሾፕ ስልጠናዎችን በግሉ መሰልጠኑ አሁን ለሚሠራው ሥራ ከፍተኛ እገዛ አድርጐለታል፡፡
የሥራ ፍቅሩ ምን እንደሚመስል ተጠይቆ በሰጠን ምላሽ፡- “ሥራ መሥራት በጣም ነው የምወደው” ሲልም ለሥራ ያለውን ፍቅር ይገልጻል፡፡
ሥራ አለ ከተባለ በቅድሚያ ራሱን አዘጋጅቶ ይጠብቃል፡፡ የሥራ ሰዓቱን ሳያባክን በአግባቡ ይጠቀማል፡፡ ጠዋት ቀደም ብሎ ገብቶ ከሰዓት መጨረሻ ላይ ይወጣል፡፡ የጀመረውን ሥራ ሳይጨርስ መውጣት አይፈልግም፡፡ የፈጠራ ሥራዎችን መሥራት ይቀናዋል፡፡ በዚሁም በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ተግባራትን ፈጥሮ በመሥራት ለተሸላሚነት በቅቷል፡፡
በሬዲዮ ክፍል በሚሠራበት ወቅት በውሃና በንፅህና ዙሪያ የሚሠራ ወሽ /WASH/ ተብሎ የሚጠራ ድርጅት ባዘጋጀው ውድድር በንፅህና ዙሪያ አንድ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅቶ በመወዳደር ሁለተኛ ወጥቶ ዘመናዊ ኮምፒዩተር (ላፕቶፕ) ተሸልሟል።
በሌላ ጊዜ ደግሞ በዚሁ ፕሮግራም በፎቶግራፍ ተወዳድሮ 3ኛ በመውጣት አንድ ዘመናዊ የእጅ ስልክ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ ይህም በቀን መቁጠሪያና በድርጅቱ ጆርናል ላይ ወጥቷል።
ለ3ኛ ጊዜ የኢትዮጵያ መድን ድርጅትን የማስተዋወቅ ኘሮግራምን በጥሩ ሁኔታ አዘጋጅቶ በመወዳደር ከመላው ኢትዮጵያ 1ኛ ወጥቶ እጅግ ዘመናዊ የግል ኮምፒዩተር (ላፕቶፕ) ተሸልሟል፡፡
የዋሽ ድርጅት ተሳትፎውን ግምት ውስጥ በማስገባት አንድ ተጨማሪ ኮምፒዩተር ለመስሪያ ቤቱ (ደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት) ሸልሟል፡፡
በአጠቃላይ በተቋሙ ቆይታው አንጋፋ እስከመባል የደረሰው ጋዜጠኛ ገናናው፣ ለረጅም ጊዜያት ስለቆየበት ጋዜጣ አንስተንለት ነበር። የአሁኑንና የቀድሞውን የጋዜጣ ይዘት እንዴት ታነፃፅራለህ? ብለን ላቀረብንለት ጥያቄ የሰጠን ምላሽ፡-
“የአሁኑ የገፅ ብዛት ጨምሯል፡፡ ከ16 ገጽ ወደ 24 ገፅ ከፍ ብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት አርቲክሎቹ ጥሩ አርትኦት ተደርጐባቸው የሚወጡ በመሆናቸው አንባቢው ሲያነብ ምንም ቅር አይለውም፡፡
“ድሮ ጋዜጣ ላይ ከፍተኛ የሰው እጥረት በመኖሩ ጽሑፎች ላይ ችግር ስለሚያጋጥም የጥራት ክፍተት ነበረበት፡፡ በአንጻሩ የአሁኑ ንጋት ጋዜጣ አርቲክሎቹ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ስለሚለጠፉ አወቃቀራቸውና አፃፃፋቸው እየተደራጀ መጥቷል፡፡
“በበለጠ ሁኔታ የተሻለ ይዘት እንዲኖረው ተገቢ የበጀት እገዛ ሊደረግለት ይገባል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ጋዜጣውን ተደራሽነቱን ለማስፋት አዙዋሪዎች እጅ የሚገባበት መንገድ መፈጠር አለበት፡፡” ብሏል፡፡
ጋዜጠኛ ገናናው ስለግል ባህሪው ሲናገር፡- “አኩራፊ አይደለሁም፡፡ ከሁሉም ጋር ተግባብቶና ተስማምቶ የመሥራት ባህሪ አለኝ” በማለት ገልጿል፡፡
ጋዜጠኛው ወደ ትዳር ዓለም የገባው 1986 ዓ.ም ሲሆን የሁለት ሴትና የሁለት ወንድ፣ በድምሩ የ4 ልጆች አባት ነው።
የመጀመሪያዋ ሴት ልጁ በአካውንቲንግ የትምህርት ዘርፍ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቃ በመንግስት ባንክ በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡ ሁለተኛው ወንድ ልጁ እንዲሁ በአካውንቲንግ ትምህርት ዘርፍ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቆ በአንድ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ማህበር ውስጥ ረዳት ሒሳብ ሹም ሆኖ ይሠራል።
3ኛው ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በዲፕሎማ ተመርቆ የኤሌክትሪክ ዝርጋታ በግሉ ይሠራል። 4ኛዋና የመጨረሻ ሴት ልጁ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ የትምህርት ክፍል የ5ኛ ዓመት ተማሪና ዘንድሮ ተመራቂ ነች፡፡
More Stories
በ2030 ደህንነቱ የተጠበቀ መጸዳጃ ቤት ለሁሉም
ኮንፈረንስ ቱሪዝም
የትራምፕ “ትራይፌክታ” ጣምራ ሥልጣን