ኮሌጆች በዕውቀትና ክህሎት የበለፀገ ትውልድ በማፍራት ችግር ፈቺ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማበርከት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለፀ

ኮሌጆች በዕውቀትና ክህሎት የበለፀገ ትውልድ በማፍራት ችግር ፈቺ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማበርከት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለፀ

በስልጤ ዞን የሌራ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ለሶስተኛ ዙር አስመርቋል።

የሌራ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪ ኮሌጅ ዲን ሸምሱ ለደጋ እንደገለጹት ውጤት ተኮር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ቁልፍ መሳሪያ ነው ብለዋል።

ኮሌጁ ብቁ፣ ተወዳዳሪና ሥራ ፈጣሪ ዜጋ በማፍራት ችግር ፈቺ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ ገበያው የሚፈልገውን የሰው ኃይል በማፍራት የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኮሌጁ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በመማር ማስተማር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ላለፉት 8 ዓመታት በመካከለኛና በዝቅተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አመላክተዋል።

በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት በስልጤ ዞን የምዕራብ በርበሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ራህማቶ ሹክራቶ በበኩላቸው ትምህርት ድህነትንና ኋላቀርነትን የምናጠፋበትና የስልጣኔ ቁንጮ ላይ ለመድረስ ቁልፍ መሳሪያ በመሆኑ ሀገራችን ኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ፍትሀዊነትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በርካታ የለውጥ ስራዎችን እያከናወነች ነው ብለዋል።

የሌራ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪ ኮሌጅ ከጊዜ ወደ ጊዜ በገበያው ተፈላጊ የሆኑ የሙያ ዘርፎች ላይ የስልጠና አድማሱን በማስፋትና አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት ወጣቶች የሙያ ባለቤቶች እንዲሆኑ ከማስቻሉም ባለፈ ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በምረቃ ፕሮግራም በክብር እንግድነት የተገኙት የስልጤ ዞን ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አቶ ፈድሉ ካድር በበኩላቸው ሀገራችን ባለፉት ዓመታት በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስብራቶችን በማቅናት በአዳዲስ እሳቤዎችና እይታዎች ተጨባጭ ለውጦችን በማድረግ የድህነትንና ኋላቀርነት መቀየር የሚችሉ በርካታ ፕሮጀክቶች ተጀምረው በራስ አቅምና ዕውቀት ለውጤት የበቁበት ነው ብለዋል።

ሀገሪቱ በቂ የሰለጠነና በራሱ የሚተማመን ከቴክኖሎጂ ጋር ራሱን የሚያላመድ የኢኮኖሚ ሽግግሩን የሚያፋጥን ዜጋ ለማፍራት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጿል።

ባለፉት አመታት የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጆችን ተደራሽ በማድረግ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ስራዎች የተሰሩ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው ከኮሌጆች ስልጠናው የሚወጡ ዜጎች በሰለጠኑበት የሙያ መስክ የመንግስትን ስራ ሳይጠብቁ በግልና በጋራ በመስራት ሀብት ማፍራት መጀመራቸው የሚደነቅ ተግባር ነው ብለዋል።

የሌራ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪ ኮሌጅ በ3ተኛው ዙር ምራቃ በተለያዩ የሙያ መስኮች በደረጃ 2 እና 4 በመደበኛ መርሐ-ግብር ያሰለጠናቸውን ወንድ 79 ሴት 93 በድምሩ 172 ተማሪዎችን አስመርቋል።

የእለቱ ተመራቂዎች በበኩላቸው በተመረቁበት የሙያ ዘርፍ ስራ ፈላጊ ሳይሆን ስራ ፈጣሪ በመሆን ማህበረሰቡን ብሎም ሀገራቸውን በቆራጥነት ለማገልገል መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

በምረቃ ፕሮግራሙ የሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ አወል ሻንጎ ጨምሮ ተመራቂ ተማሪዎች የተመራቂ ተማሪ ቤተሰቦችና ሌሎች ጥር የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ: ሙጅብ ጁሃር – ከሆሳዕና ጣቢያችን