በ2030 ደህንነቱ የተጠበቀ መጸዳጃ ቤት ለሁሉም
በመለሰች ዘለቀ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአለም አቀፍ ደረጃ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ሰዎች ደህንነቱ የተጠበቀ የንፅህና አጠባበቅ እጦት እንዳለባቸው ገልጿል። በመሆኑም “ደህንነቱ የተጠበቀ መጸዳጃ ቤት ለሁሉም ሰው በ2030” የሚለውን መርህ እውን ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡
እንደ አፍሪካ ኒውስ ዘገባ የዓለም የመፀዳጃ ቤት ቀን በተለይ በአፍሪካ ውስጥ ደህንነታቸውና ንጽህናቸው የተጠበቁ መጸዳጃ ቤቶች አስፈላጊነት ላይ ትኩረት አድርጓል።
እንደ ናይጄሪያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኒዠር፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ቡርኪናፋሶ እና ቻድ ባሉ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ንጽህናቸው የተጠበቀ መጸዳጃ ቤቶች ተደራሽነት ችግር በመኖሩ ሰዎች ከቤት ውጭ ይጸዳዳሉ፡፡ ባለፉት አስር አመታት ወደ 20 የሚጠጉ የአፍሪካ ሀገራት በኮሌራ ወረርሽኝ ተጎድተዋል።
የዘንድሮው የመጸዳጃ ቤት ቀን ሽንት ቤቶች በግጭቶች፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በተፈጥሮ አደጋዎች እና በስርዓት ቸልተኝነት ሳቢያ በንፅህና አጠባበቅ ላይ ያለውን ስጋት አፅንዖት ይሰጣል።
“በ2030 ደህንነቱ የተጠበቀ መጸዳጃ ቤት ለሁሉም” ከዘላቂ ልማት ግብ አንዱ ነው። ነገር ግን ይህንን ግብ እስከ አውሮፓዊያኑ 2030 ድረስ በቀሩት አምስት ዓመታት ማሳካት ይቻላል ወይ? የሚለው አጠያያቂ ጉዳይ ነው፡፡
በዓለማችን 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሰዎች ደህንነቱ ያልተጠበቀ መጸዳጃ ቤት ይጠቀማሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በመላው አፍሪካ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለተላላፊ በሽታዎች ይዳረጋሉ፡፡
በየዓመቱ ህዳር 19 ቀን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አማካኝነት የዓለም የመፀዳጃ ቀን ይከበራል፡፡ በ2024 በአየር ንብረት ለውጥ፣ በጦርነት እና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ሰዎች ደህንነቱ የተጠበቀና ንጽህና ያላቸውን መጸዳጃ ቤቶች የማግኘት አቅማቸው እየተስተጓጎለ ነው። ከዚህም የተነሳ በርካታ ሰዎች የኮሌራ ወረርሽኝን ጨምሮ ለተላላፊ በሽታዎች የመጋለጥ እድላቸው ጨምሯል፡፡
ሜዳ ላይ መጸዳዳት በበሽታ የመጋለጥ እድሉ ከፍተኛ ነው። መጸዳጃ ቤት አለመኖር እና ንጽህና ባልተጠበቀ የመጸዳጃ ቤት ችግር ምክንያት ሜዳ ላይ መጸዳት አይነምድር የውሃ ምንጮችን ሊበክል ይችላል፡፡ ይህ በውሃ እና በምግብ ሰንሰለት ውስጥ በሰዎች እና በከብቶች ላይ የውሃ ወለድ በሽታዎችን ያሰራጫል።
በቅርቡ በኢንዱስትሪ ማይክሮባዮሎጂስት ሄለን ኦንያካ እና በሕዝብ ጤና ማይክሮባዮሎጂስት ኦሞሎሉ ፋጉንዋ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው፣ በውጭ በመፀዳዳት ምክንያት የሚመጡ በሽታዎች ፀረ ተሕዋስያን መድሃኒቶችን የመቋቋም አቅም አላቸው። መድሃኒቶችን የመቋቋም ችሎታ ያላቸው ባክቴሪያዎች ስለሚሰራጩ መድሃኒቶቹ የመፈወስ አቅም አይኖራቸውም፡፡
ባለፉት አስር አመታት ወደ 20 በሚጠጉ የአፍሪካ ሀገራት በርካታ ሰዎች በኮሌራ ወረርሽኝ ተጎድተዋል። በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል። ኮሌራ የሚተላለፈው በተበከለ ውሃ ወይም ምግብ አማካኝነት ሲሆን የሚከሰተውም የንጽህና ጉድለት ያላባቸው አካባቢዎች ነው።
በተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት መጠለያ ካምፖች ውስጥ የሚኖሩ ተፈናቃዮች የጋራ መጸዳጃ ቤት ስለሚጠቀሙ ለአደጋው የተጋለጡ ናቸው። የማይክሮባዮሎጂ ባለሙያ እና ተላላፊ በሽታዎች ተመራማሪው ሳሙኤል ካሪዩኪ፣ የአፍሪካ መንግስታት በተጨናነቁ አካባቢዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ እና የመጸዳጃ ቤት ለማቅረብ መጠነኛ ሙከራዎችን እያደረጉ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን ገልጸዋል።
በደቡብ አፍሪካ ሃማንስክራል ቀጠና በ2023 የኮሌራ ወረርሽኝ የ47 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። ይህም የቧንቧ ውሃ በኮሌራ በመበከሉ ምክንያት ነው። በሀገሪቱ በኢንዱስትሪ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወንዞች የንፅህና አጠባበቅ ስርዓቶች መበላሸታቸውን ተከትሎ በአካባቢው የተላላፊ በሽታዎች ስርጭት እየጨመረ መጥቷል።
የሀገሪቱ የውሃ አስተዳደር ኤክስፐርት አንጃዱ ፕሌሲስ ኮሌራን ለመከላከል ግለሰቦች እጃቸውን በውሃና በሳሙና እንዲታጠቡ ማበረታታት ብቻ በቂ እንዳልሆነ ተገንዝበዋል። እያንዳንዱ ሰው ለመጠጥ፣ ለመታጠብ፣ ለመጸዳጃ ቤት፣ ምግብ ለማብሰል፣ ልብስ ለማጠብ እና የቤቱን ንጽህና ለመጠበቅ በቂ ንጹህ ውሃ ከሌለው የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱ ይቀጥላል። የዓለም ጤና ድርጅት በቀን ቢያንስ ከ50 እስከ 100 ሊትር ውሃ ለአንድ ሰው እንደሚያስፈልግ ገልጿል።
በናይጄሪያ ብዙዎቹ የጋራ መጸዳጃ ቤቶች የሚጠቀሙ በመሆናቸውና ደካማ የፍሳሽ ማስወገጃ ዘዴዎች ምክንያት የተላላፊ በሽታዎች ስርጭት አስጊ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
የመፀዳጃ ቤት እጦት ለናይጄሪያዊያን በተደጋጋሚ ከአየር ንብረት ለውጥ፣ ከውሃ ብክለት እና ከእርሻ መሬት መበከል የበለጠ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።
በደቡብ አፍሪካ 65 በመቶው ህዝብ ብቻ ንጽህናቸው የተጠበቀ መጸዳጃ ቤት ያላቸው ሲሆን 32 በመቶው ደግሞ የጉድጓድ መጸዳጃ ቤቶችን ይጠቀማሉ። ከድርቅ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው የውሃ እጥረት ምክንያት ለመንግስት ንጽህና የተጠበቀ መጸዳጃ ቤቶችን ተደራሽ ማድረግ አዳጋች ሆኗል።
በሲልቨር ከተማ ካዬሊትሻ ውስጥ ከ3 ሺህ በላይ ቤተሰቦች ንጹህ ያልሆኑ መጸዳጃ ቤቶችን ለመጠቀም ወይም በመስክ አፋቸውንና አፍንጫቸውን በመሸፈን ለመጠቀም ተገድደዋል።
ብዙ መጸዳጃ ቤቶች በር፣ የውኃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ወይም መቀመጫ የላቸውም። በአካባቢያቸው የመጠጥ ውሃ ከሽንትና ከቆሻሻ ውሃ ጋር የተቀላቀለ በመሆኑ ለጤና ጠንቅ ያደርገዋል።
አንዳንድ ነዋሪዎች በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ባልዲዎችን ተጠቅመው ወይም መሬት ቆፍረው ሽንት ቤት መጠቀም ጀምረዋል፡፡ በዚህ ምክንያት አካባቢያቸው በበሽታው እየተበከለ እንደሆነ አንዳንድ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ከትዳር አጋሯ እና ከሁለት ልጆቿ ጋር በመጸዳጃ ቤት አቅራቢያ የምትኖረው አሳንዳ ሌንጌሲ ስለ ጠረኑና ስለ ዝንቡ አማርራለች።
“ሽታው በበጋ እየባሰ ይሄዳል፣ ከዚህም የተነሳ ቀን ቀን በጓደኛዬ ቤት አሳልፋለሁ” ትላለች።
የከተማው የዊኒ ማዲኪዜላ ሳንኮ ቅርንጫፍ ሊቀ መንበር ሉባባሎ ሙሱቱ እንዳሉት “በፍርስራሽ የተከበቡ” እና በአሁኑ ጊዜ ተደራሽ ካልሆኑት በስተቀር አብዛኛዎቹ መጸዳጃ ቤቶች ተስተካክለው እንደነበር ገልፀው ነገር ግን የተሻሻሉ መጸዳጃ ቤቶች እንደሚገኙ ተናግረዋል። የመፀዳጃ ቤቶቹ መበላሸት በአንዳንድ ግለሰቦች ድርጊት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
“እንደ አለመታደል ሆኖ ከተበላሹ መጸዳጃ ቤቶች በተጨማሪ ብዙ ጊዜ ሌሎች ቆሻሻዎች ወደ መጸዳጃ ቤት ተጥለው ህብረተሰቡ እንዳይጠቀሙበት እናደርጋለን” ብለዋል፡፡
More Stories
“ኩርፊያ እና ንትርክ አልወድም” – ጋዜጠኛ ገናናው ለማ
ኮንፈረንስ ቱሪዝም
የትራምፕ “ትራይፌክታ” ጣምራ ሥልጣን