በከተማው የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን ዕውን ለማድረግ የተሰበሰበውን ሀብት በቁጠባና በግልጸኝነት መጠቀም እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 06/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሀዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ የሚሰሩ የልማት ፕሮጀክቶች ዕውን ለማድረግ የተሰበሰበውን ሀብት በቁጠባና በግልጸኝነት መጠቀም እንደሚገባ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
በሀዲያ ዞን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ጽ/ቤት የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና የ2018 ዓ.ም ዕቅድ ዙሪያ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚመክር ጉባኤ አካሄዷል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ ከተማው በራሱ ገቢ የሚተዳደር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተሰበሰበውን ገቢ በቁጠባና በግልጸኝነት መጠቀምና ማስተዳደር እንደሚገባ ተናግረዋል ።
ጽ/ቤቱ በክልሉ፣ በዞኑና በከተማው አስተዳደሩ የተሻለ አፈጻጸም በማግኘቱ ተሸላሚ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም ተግባር ለባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል ።
በከተማው የሚሰሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተፈጻሚ እንዲሆኑ የፋይናንስ ተቋም የፕሮጀክቶችን አፈፃፀም መከታተል እንደለበት አሳስበዋል ።
የሆሳዕና ከተማ ፋይናንስ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ገነት ሰለሞን እንደገለፁት በተጠናቀቀው በጀት አመት በከተማው የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ውጤት ተኮር ዕቅድ በማዘጋጀት ሀብትን በቁጠባ በመምራት የተሻለ አፈጻጸም ማምጣት መቻሉን ገልጸዋል ።
በበጀት ዓመቱ አፈፃፀም ፋይናንስ ጽ/ቤቱ በክልሉ፣ በዞንና በከተማ ደረጃ ግምባር ቀደም በመሆኑ የዋንጫ ተሸላሚ መሆኑን ጠቁመዋል ።
ለዚህም የጽ/ቤቱ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ይበልጥ በትጋት እደሚሰራ ተናግረዋል ።
በከተማው ለበርካታ አመታት ሳይከፈል ቆይቶ የነበረውን የመንግሥት ሰራተኞች የጡረታ ዕዳ ለማህበራዊ ዋስትና 230 ሚሊዮን ብር መክፈል መቻሉን ገልጸዋል ።
ለበርከታ አመታት ሳይወገዱ የቆዩ የአገልግሎት ጊዜያቸውን ያበቁ ተሽከርካሪዎችን ሙሉ በሙሉ በማስወገድ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግስት ገቢ መደረጉን ጠቁመዋል።
ከተማውን “ስማርት ሲቲ” ለማድረግ በሚሰሩ ኮሪደር ልማት፣ የሕዝብ ፋርማሲ፣ የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገዶችና ሌሎች ፕሮጀክቶች ተፈጻሚ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።
ኃላፊዋ አክለው በዚህ አመትም የሚሰበሰበውን ሀብት በተገቢው በመጠቀም፥ በግልጸኝነት ለታለማው ዓላማ ማዋል እንዲቻል በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል ።
በሪፖርቱ አጠቃላይ በተቋሙ የተከናወኑ ተግባራት ቀርበው ደካማና ጠንካራ ጎኖችን በመምገም የቀጣይ ስራ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ከመድረኩ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል ።
በመጨረሻም የጽ/ቤቱ ተግባር እንዲሳካ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አመራሮች እና ባለሙያዎች ዕውቅና በመስጠት የምክክር ጉባኤው ተጠናቋል ።
ዘጋቢ: ታምራት አለሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
ኮሌጆች በዕውቀትና ክህሎት የበለፀገ ትውልድ በማፍራት ችግር ፈቺ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማበርከት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለፀ
በጎፋ ዞን ኢሲፔ ዲቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የገበሬዎች ሁለገብ ህብረት ሥራ ዩኒየን ካፒታሉን 62 ሚሊየን ብር በማድረስ ዓመታዊ ትርፉ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ መሆኑን አስታወቀ
የአየር ፀባይ መረጃ ስርጭት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ