በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደረጃ 19ኛዉ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በነገዉ ዕለት በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አቡቶ አኒቶ ገለፁ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደረጃ 19ኛዉ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በነገዉ ዕለት በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አቡቶ አኒቶ ገለፁ

በዓሉን አስመልክቶ አፈ ጉባኤዉ ለደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት መግለጫ ሰጥተዋል።

“ሀገራዊ መግባባት፤ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል 19ኛዉ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደረጃ በነገዉ ዕለት በየም ዞን ሳጃ ከተማ በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር የገለፁት የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አቡቶ አኒቶ፥ በዓሉ በክልሉ ከቀበሌ ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር መቆየቱን ተናግረዋል።

በነገዉ ዕለትም የፌደራል ስርዓቱንና የእርስ በርስ ትስስርን በሚያጠናክር መልኩ በድምቀት በሳጃ ከተማ በዓሉ ይከበራል ያሉት አቶ አቡቶ አኒቶ፥ በዕለቱ የፌደራል ስርዓቱ ላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና መፍትሔዉ ላይ ሰነድ ቀርቦ ዉይይት ይደረጋልም ብለዋል።

በበዓሉ ላይ የህዝቦችን ትስስር ለማጠናከር ከአጎራባች ክልሎችም ጭምር እንግዶች እንደሚገኙ አፈ ጉባኤዉ ጠቅሰዋል።

የበዓሉ መከበር ብሔሮችና ብሔረሰቦች ባህሎቻቸዉን አጉልተዉ እንዲያሳዩ ዕድል እንደሚሰጣቸዉ የተናገሩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አቡቶ አኒቶ፥ ክልሉ አዲስ በመሆኑ በዓሉን ዘንድሮ ለ2ኛ ጊዜ እያከበረ ቢሆንም ከዚህ በፊት እስከ 18ኛ ጊዜ የተከበሩ በዓላት ብሔሮችና ብሔረሰቦች ማንነታቸዉ እንዲተዋውቁና በዓሉ በሚከበርባቸዉ ቦታዎች መሰረተ ልማት እንዲስፋፉ ዕድል መፍጠሩንም አብራርተዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አቡቶ አኒቶ ለ19ኛዉ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትንም አስተላልፈዋል።

19ኛዉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “ሀገራዊ መግባባት፤ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ ህዳር 29/2017 ዓ.ም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባምንጭ ከተማ ይከበራል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደረጃ በነገዉ ዕለት የሚከበረዉን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በቀጥታ ስርጭት የሚያስተላልፍ ይሆናል።

ዘጋቢ፡ ድልነሳዉ ታደሰ