በልዩ ወረዳው ትምህርት ቤቶች ልምድና ብቃት ባላቸዉ የትምህርት አመራሮች እንዲመሩ በማድረግ ባለፉት አመታት በትምህርት ዘርፍ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለፀ
ይህ የተገለፀው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት የመጀመሪያው ሴክቶሪያል ጉባኤውን “የላቀ ትጋት ለትምህርት ጥራት” በሚል መርህ በወልቂጤ ከተማ ባካሄደበት ወቅት ነው።
በመድረኩ የተገኙት የቀቤና ልዩ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ እና የፍትህ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አብድልማሊክ አብደላ እንደገለፁት፤ በልዩ ወረዳዉ የትምህርት ዘርፉን ዉጤታማ ለማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጡ የትምህርት ማሻሻያ ፖሊሲዎች ትግበራ ቢደረግም ባለፉት አመታት በዘርፉ የዉጤት ስብራት አጋጥሟል።
ስለሆነም በዘርፉ ያጋጠሙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የመማር ማስተማሩ ሂደት ምቹ እና ሳቢ ከማድረግ እንዲሁም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ከማሻሻል ጀምሮ ትኩረት ሊሰጠዉ እንደሚገባ ምክትል አስተዳዳሪዉ አሳስበዋል።
የህብረተሰቡ ተሳትፎ በትምህርት ጥራት ላይ ያለዉ አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ አብድልማሊክ፤ በተለይም ተማሪዎች እና መምህራን እምቅ አቅማቸዉን በትምህርት ጥራት ላይ ማዋል እንደሚገባቸዉ አስገንዝበዋል።
የቀቤና ልዩ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አህመድ ሀሰን በበኩላቸው፤ በልዩ ወረዳዉ ጥራት ያለዉ ትምህርት ተደራሽ ለማድረግና በስነ ምግባር የታነጸ አገር ተረካቢ ዜጋ ለመፍጠር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በተያዘዉ የ2017 የትምህርት ዘመን ከ16 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመቀበል የመማር ማስተማር ስራ መጀመሩን የገለፁት ሀላፊዉ፤ ትምህርትን ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ በዘርፉ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ባለፉት አመታት በትምህርት ዘርፉ ላጋጠሙ ችግሮች መፍትሄ ለማምጣት ትምህርት ቤቶች ብቃት ባላቸዉ አመራሮች እንዲመሩ ለማድረግ ከክልሉ ጋር በተሰሩ ቅንጅታዊ ስራዎች አብዛኛዉ ትምህርት ቤቶች ላይ አቅም ያላቸዉ አመራሮች ተመድበዋል ነዉ ያሉት።
በ2016 የትምህርት ዘመን በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ ለትምህርት ልማት ማዋል መቻሉን ያወሱት ሀላፊው በትምህርት ዘመኑ በተሰጠው ክልል አቀፍ ፈተና የተማሪዎች ዉጤት የተሻለ እንደነበር ገልጸዋል።
በብሄራዊ ፈተና ያጋጠሙ የዉጤት ማሽቆልቆል ችግሮችን ለመቅረፍም ጽ/ቤቱ ከሆሳዕና መምህራን ትምህርት ኮሌጅ እና ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር እየሰራ ያለዉን ቅንጅታዊ ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ለመፍጠር አዳሪ ትምህርት ቤት ለመገንባት ፕሮጀክት ተቀርፆ ከቀቤና ልማት ማህበር ጋር እየተሰራ እንደሚገኝም በማመላከት ለዚህም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
በቀቤኤንሲና ቋንቋ ትምህርት መሰጠት ከተጀመረ 25 አመታት ያለፈዉ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት አለመቻሉን በማንሳት፤ አሁን ላይ ለዘርፉ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በጥናት ተለይተው ቋንቋዉን ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የወልቂጤ ዩንቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ቸርነት ዘርጋ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲዉ በቀቤና ልዩ ወረዳ በማህበረሰብ አገልግሎት በተለይም በትምህርት ዘርፍ ተማሪዎች ለክልል እና አገር አቀፍ ፈተናዎች ብቁ እንዲሆኑ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ በመግለፅ ይህንኑ አጠናክሮ ይቀጥላል።
በጉባኤዉ የተሳተፉ አካላት በሰጡት አስተያየት በልዩ ወረዳዉ የትምህርት አገልግሎት መሰጠት ከተጀመረ በርካታ አመታት መቆጠሩን በመግለፅ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ መምጣታቸውን አመላክተዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ ሁሉም የድርሻዉን ሊወጣ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ በ2016 የትምህርት ዘመን የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ትምህርት ቤቶች እና ተቋማት የእዉቅናና የምስጋና ሰርተፍኬት የተሰጣቸዉ ሲሆን ከትምህርት ቤቶች ጋር የግብ ስምምነትም ተደርጓል።
ዘጋቢ፡ ሪያድ ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
ተቀራርቦ በጋራ መሥራት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያዝ ተጠቆመ
የጀፎረ ባህላዊ አውራ መንገድን ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ተጠቆመ
በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የማስተማር አቅም ግንባታ ለትምህርት ባለድርሻ አካላት ስልጠና ተሰጠ