ኦክስሌድ ቻምበርሌን በአርሰናል ልምምድ መስራት ጀመረ

ኦክስሌድ ቻምበርሌን በአርሰናል ልምምድ መስራት ጀመረ

እንግሊዛዊው የፊት መስመር ተጫዋች ኦክስሌድ ቻምበርሌን በቀድሞ ክለቡ አርሰናል ልምምድ መስራት መጀመሩ ተገልጿል።

የ32 ዓመቱ ተጫዋች ተክለ ሰውነቱን ለማስተካከል ከአርሰናል ከ21 ዓመት በታች ቡድኑ ጋር ልምምዱን እየሰራ እንደሚገኝ ስካይ ስፖርት አስነብቧል።

ኦክስሌድ ቻምበርሌን እንደ አውሮፓውያኑ በ2017 ወደ ሊቨርፑል ከመዛወሩ በፊት ለሰሜን ለንደኑ ክለብ ዋናው ቡድን ወደ 200 የሚጠጋ ጨዋታ ተሰልፎ አከናውኗል።

በኋላም እስካሁን ድረስ የክለቡ ክብረወሰን በሆነ ሽያጭ በ35 ሚሊዮን ፓውንድ ለሊቨርፑል መፈረሙ ይታወሳል።

ከሊቨርፑል ጋር የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ማሸነፍ የቻለው ቻምበርሌን ሊቨርፑል ለቆ ለቱርኩ ክለብ ቤሲክታሽ በመፈረም ተጫውቶ ማሳለፉ አይዘነጋም።

ተጫዋቹ በቤሲክታሽ ያለው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ክለቡን ባሳለፍነው ክረምት ለቆ ነፃ ሆኖ ይገኛል።

ቻምበርሌን አሁንም ቢሆን ከሌሎች ሀገራት የዝውውር ጥያቄ ቢቀርብለትም በእንግሊዝ መቆየትን ምርጫው ማድረጉን ተከትሎ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ ተጠቁሟል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ