“ሃገሬን ከማጣ ህይወቴን ባጣ እመርጣለሁ” – መሪጌታ መኮንን ሀረገ-ወይን

“ሃገሬን ከማጣ ህይወቴን ባጣ እመርጣለሁ” – መሪጌታ መኮንን ሀረገ-ወይን

በአብርሃም ማጋ

ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ የገጠሟትን ፈተናዎች በልጆቿ ብርቱ ትግል መክታ ለዛሬ መብቃቷን ዓለም የሚያውቀው እውነታ ነው። ከእነዚህ ብርቱ ዜጎች መካከል የሃይማኖት መሪዎች፣ መምህራንና የተለያዩ አገልጋዮች እንደሚገኙበት የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡

የዛሬው ባለታሪካችንም መሰል ታሪክ ያላቸው መሪጌታ ናቸው፡፡ ባለታሪካችን መሪጌታ መኮንን ሃረገ-ወይን ይባላሉ፡፡ “ሀይማኖትን ይዞ ለሀገር መዋጋት ለድል ያበቃል እንጂ ለሽንፈት አይዳርግም” ሲሉ የአድዋ ድልን ለአብነት በማንሳት ሃሳባቸውን ማጋራት ይጀምራሉ፡፡ ይህን ማድረግ በሃገራችን ከጥንት ጀምሮ የተለመደና ተያይዞ የመጣ ቅርስ መሆኑንም ያነሳሉ፡፡

እሳቸውም የአባቶቻቸውን ታሪክ ሶማሊያ ሃገራችንን በወረረች ጊዜ ካራማራ በመዝመት ደግመውታል፡፡ ገና በወዝ አደርነት ሲሰሩ ለሚሊሺያነት ሲመለመሉ ቆርጠው የመነሳታቸው ጉዳይም ለሃገራቸው ካላቸው ከፍተኛ ፍቅር ነበር። ምክንያቱም ሃገር ከሌለ ምንም ነገር እንደሌለ ጠንቅቀው ያውቃሉና፡፡ ሃገር ከሌለ ሃይማኖት፣ ሃብት፣ ልጅ፣ ሥራ፣ ምግብ፣ መጠለያ፣ መማር፣ መመራመር፣ መነገድ፣ መኖር…ወዘተ የማይታሰብ እንደሆነ ተረድተዋል፡፡

በዚህም የወቅቱን ጠላት ለመመከት በቆራጥነት ግንባር መዝመታቸውንና ሀገራቸውን ነፃ ማውጣታቸውን ከአንደበታቸው ለመረዳት ችለናል፡፡ ለመግቢያነት ይህንን ካልን ዘንዳ ስለምርጥ ተሞክሯቸው ልናስነብባችሁ ወደናል መልካም ንባብ፡፡

መሪጌታ መኮንን ሃረገ-ወይን በቀድሞው አጠራር በጐጃም ጠቅላይ ግዛት፣ በደብረማርቆስ አውራጃ በቢቡኝ ወረዳ፣ በደብረ መድሃኒት ቀበሌ በ1943 ዓ.ም ነው የተወለዱት፡፡ ዛሬ ላይ የ74 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ ናቸው፡፡

ፊደል መቁጠር የጀመሩት በአካባቢው በሚገኝ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን ሲሆን የቄስ ትምህርት የገቡት ገና በ7 ዓመታቸው ነበር፡፡ ውዳሴ ማሪያም፣ ዳዊት፣ ፆመ ድጓ፣ አርያም፣ የላይ ቤት፣ አቋቋም፣ ዝማሬ ተምረው አጠናቀዋል። ለዚህም ምክንያቱ በወቅቱ በአካባቢያቸው ከመደበኛ ትምህርት ይልቅ ትኩረት ይሰጥ የነበረው ለሀይማኖት/ቄስ/ ትምህርት በመሆኑ ነበር፡፡

ከዚያም በ1951 ዓ.ም ከቅኔ ትምህርት በተጨማሪ ሸላል ገብርኤል ወረዳ ሽመና ሚካኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ ለ4 ዓመታት ተከታትለው ድቁና ከወሰዱ በኋላ ወደ ሃገር ቤት ተመልሰዋል።

እንደተመለሱም በቂርቆስ ቤተክርስቲያን ውስጥ በድቁናቸው ማገልገል ጀመሩ፡፡ በወቅቱ እድሜያቸው ለአቅመ አዳም በመድረሱ በቤተክርስቲያን ህግ በሥርዓተ ቤተክርስቲያን /ተክሊል/ ትዳር መሠረቱ፡፡

በቤተክርስቲያኑ ለተወሰኑ ዓመታት የነፃ አገልግሎት/ያለክፍያ/ እየሰጡ ሁለት ወንድ ልጆች ከወለዱ በኋላ ቤተሰቦቻቸውን ጥለው በ1965 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ገቡ፡፡

ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ያስገደዳቸው ቤተሰባቸውን ማስተዳደር የሚያስችል በቂ ገቢ ስለሌላቸው ቋሚ ሥራ ፍለጋ እንደሆነ ይናገራሉ። ምኞታቸው ተሳክቶላቸው በኢትዮጵያ እርሻ ዘዴ /ማስፋፊያ/ መሥሪያ ቤት በ85 ብር ደመወዝ በጥበቃ ሥራ ተቀጠሩ፡፡ ከዚህም ጐን ለጐን በኡራኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ የድቁና አገልግሎት ይሰጡም ነበር፡፡

በመስሪያ ቤቱ በተቀጠሩበት ሥራ መደብ ለ3 ዓመታት ያህል ከሠሩ በኋላ በ1968 ዓ.ም መስሪያ ቤቱን ቀይረው በተሻለ ደመወዝ የሚቀጠሩበት እድል አጋጠማቸው፡፡

አዲሱ መስሪያ ቤት ብሔራዊ ሃብት ሚኒስቴር ሲሆን መስሪያ ቤቱ ባወጣው የቅጥር ማስታወቂያ መሠረት ተወዳድረው ፈተናውን በማለፋቸው በቋሚነት ተቀጥረው ወደ ሲዳሞ ክ/ሀገር፣ ሲዳማ አውራጃ በሀዋሣ ወረዳ ሀዋሣ እርሻ ልማት ተመደቡ፡፡ በወቅቱ የወር ደመወዛቸውም 120 ብር ነበር፡፡ ይህም በወቅቱ ሻል ያለ ኑሮ ለመኖር የሚያስችል እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡

የሀዋሣ እርሻ ልማትም እሳቸውን በወንዶ ጢቃ አብይ እርሻ ውስጥ የንብረትና የፀጥታ ተቆጣጣሪ አድርጐ መደባቸው፡፡ በተመደቡበት ሙያ ተደስተው በትጋትና በፍቅር ለአንድ ዓመት ያህል ከሠሩ በኋላ አንድ አዲስ ክስተት ተፈጠረ፡፡

ክስተቱም በምሥራቅ በኩል የሶማሊያ መንግስት በሀገራችን ላይ የከፈተው ጦርነት ነበር። ለዚህም አርሶ አደሩና ወዝ አደሩ በሚሊሸያነት ተመልምሎ እንዲዘምት የደርግ መንግስት መመሪያ አወጣ፡፡

በመመሪያው መሠረትም እሳቸውም ከሌሎቹ ባልደረቦቻቸው ጋር ተመለመሉ፡፡ በወቅቱ ዘምተን ህይወታችን ከምናጣ አንዘምትም ብለው የሸሹና ሥራውን የለቀቁ ቢኖሩም እሳቸው ግን ቆራጥ አቋም ወስደው ለዘመቻው ዝግጁ ሆኑ፡፡

በወቅቱ ከፍተኛ የሀገር ፍቅርም ስለነበራቸው “ሃገሬን ከማጣ ህይወቴን ባጣ ይሻላል” በሚል አቋም በቆራጥነት ተመልምለው ወደ ማሰልጠኛ ገቡ፡፡

በወቅቱ አቋም ለመወሰድ የበቁት “ሃገር እናት ነች” የሚል መርህ ተከትለው እናታቸው ስትጠፋና ስትጐዳ ማየት ሰለማይፈልጉ ነበር። በዚሁም ወደ ማሰልጠኛው የገቡት ቅዱሳን የፀሎት መጽሐፍትና መስቀላቸውን ይዘው በፀሎት ነበር፡፡

በውትድርና ማሰልጠኛ ጣቢያ ለ3 ወራት ያህል ከሰለጠኑ በኋላ የወዝአደር ሚሊሺያ ሆነው ወደ ምሥራቅ ጦር ግንባር ዘመቱ፡፡ በጦር ግንባሩም በ1ኛ ወዝአደር ክ/ጦር፣ በመቶኛ ብርጌድ፣ በ1ኛ ሻለቃ፣ በ4ኛ ሻምበል አዛዥ ሆነው ተመደቡ፡፡

አዛዥነታቸውን ይዘው በአሰብ መስመር አዳይታ፣ ነጭ ሣር፣ ሚሌ፣ አልውሃ ሲሆን በገለምሶ አውራጃ ደግሞ ኮራ፣ አደልና ጨርጨር፣ አሰበ ተፈሪ፣ ዴንዲ ወረዳዎች አዝምተው እያዋጉ ተዋግተዋል፡፡

ከአዋሽ ወዲያ ባሉ አካባቢዎች በየካቲት 26/1972 ዓ.ም ላይ የሶማሊያ ጦር ሲደመሰስ የእሳቸው ጦር ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ በኋላ ላይ አካባቢው ነፃ ሲሆን ወደ ምድብ ጣቢያቸው ተመልሰዋል፡፡

በጣቢያቸው ለተወሰኑ ጊዜያት ከቆዩ በኋላ ሶማሊያ አቦ የሚባሉ ጦረኞች በአሰቦት ሥላሴ ወረዳ ጦርነት አንስተው ተመልሰው በመሄድ ገለውና ማርከው በማሸነፍ ድል ተቀዳጅተዋል፡፡ ይህ የሆነው በ1973 ዓ.ም እንደሆነም ከመግለፅ ወደኋላ አላሉም፡፡

ከዚያም ሀገራችንን ነፃ ካወጡ በኋላ ወደ አዋሽ ተመልሰው የመተሐራ ስኳርና የመርቲ የአትክልትና ፍራፍሬ ፋብሪካዎችን እየተዘዋወሩ ይጠብቁ ነበር፡፡

በአጠቃላይ በ1974 ዓ.ም ሀገሪቷ ነፃ ስትሆን መንግስት ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግምባር የሚል አዋጅ ሲያወጣ እነሱ በሌሎች ተተክተው ተመርቀው ወደ አካባቢያቸው ተመልሰዋል፡፡

በምርቃቱ ሥነ-ሥርዓት ወቅት መሪጌታ መኮንን ሀረገ-ወይን በጦርነት ወቅት ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሶስት የኒሺያን ሜዳሊያ ተሸላሚ ነበሩ፡፡ በዚህ በከባድ ጦርነት ውስጥ አሳልፈው አካላቸውን ምንም ጥይት ሳይነካቸው ተመልሰዋል፡፡

መሪጌታ ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ በወንዶ ጢቃ አብይ እርሻ ጣቢያ ወደ ቀድሞው ሥራቸው ተመልሰው መሥራት ጀመሩ፡፡ ሥራቸውን በተገቢው ከመሥራት ጐን ለጐን መደበኛ ትምህርት በሀዋሣ ከተማ በታቦር ትምህርት ቤት ገብተው እስከ 9ኛ ክፍል ተምረዋል፡፡

በሥራቸው ጠንቃቃ፣ ጠንካራ፣ ታታሪና ጐበዝ በመሆናቸው በመስሪያ ቤታቸው በተለያዩ ሃላፊነት ቦታዎችም ሠርተዋል፡፡ የወታደር ሥነ ምግባር የተላበሱ በመሆናቸው በተሰጣቸው ሥራ መደቦች ሁሉ ላይ የተሳካ ተግባራት ፈጽመዋል፡፡

መሪጌታ መኮንን ከዘመቻ መልስ እስከ 9ኛ ክፍል ከማጠናቀቃቸው ባሻገር በአውቶ መካኒክ የ6 ወር ስልጠና፣ በአግሮ መካኒክ የ1 ወር ስልጠና ወስደው የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡

በመሆኑም መደበኛ ሥራቸው ትራክተሮችንና ኮምባይነሮችን መጠገን ሲሆን በወቅቱ በንኡስ እርሻው ከሚያደርጉት ከፍተኛ የሥራ እንቅስቃሴ አንፃር የሥራ ዘመቻ የዘማች ሠራተኞች እንክብካቤና ተቆጣጣሪ በመሆን ጥሩ ሥራ ሠርተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በእርሻ ልማቱ የመሠረተ ትምህርት ንኡስ ኮሚቴ በመሆን ለ6 ዓመታት ሠርተዋል፡፡

በእርሻ ልማቱ የሠራተኛው መሠረታዊ ማህበር የዘርፍ ኮሚቴ ሊቀ መንበር፣ የሲዳሞ ክፍለ ሃገር አካባቢ ሠራተኞች ማህበር የጉባኤ አባል፣ የሀዋሣ ዙሪያ ወረዳ ሠራተኞች ማህበር የሥራ አስፈፃሚ አባል፣ የሐይቆችና ቡታጅራ አውራጃ ሠራተኞች ማህበር የጉባኤ አባል፣ የሲዳማ አውራጃ ሠራተኞች ማህበር የጉባኤ አባል ሆነው ያገለገሉባቸው የኃላፊነት ቦታዎች እንደሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ውጭም የሀዋሣ ወንዶ ጢቃ እርሻ ልማት ሠራተኞች ሠርቶ አደር ቁጥጥር ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበር በመሆን አገልግለዋል፡፡

በሐይማኖት በኩልም የወንዶ ጢቃ መድሃኒዓለም ቤተክርስቲያንን የአካባቢውን ህብረተሰብ በማስተባበር በማሰራት ረገድም ላቅ ያለ ሚና ተጫውተዋል፡፡

በዚሁም ቤተክርስቲያኗ ተሠርታ ስትጠናቀቅ የመሪ ጌታነቱን ቦታ ይዘው እስከ 1982 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል፡፡

በእነዚህ ዓመታት በሠሩባቸው ጊዜያት ባበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሁለት የኒሻን ሜዳሊያ ተሸልመዋል፡፡ መሪጌታ መኮንን ሀረገ-ወይን የተጠቀሱትን ተግባራት በመስሪያ ቤታቸው ከፈፀሙ በኋላ በ1982 ዓ.ም በዳግም ዘመቻ ጥሪ ወደ ሰሜን ግንባር ዘምተው ለሁለት ዓመታት መስዋእትነት ከፍለዋል፡፡ በ1983 ዓ.ም ኢህአዴግ ሀገሪቷን ሲቆጣጠር አሥመራ እንደነበሩ በመጥቀስ፡፡

ከዚያም የቀድሞ ጦር ወደመጡበት ሲመለሱ እሳቸው ከባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው በእግራቸው ጉዞ ጀመሩ፡፡ ቀንና ሌሊት እየተጓዙ ከአሥመራ መቀሌ ደረሱ፡፡ መቀሌ እንደደረሱ ቀይ መስቀል ማህበር የሰጣቸውን ብርድ ልብስ፣ አንሶላና ቱታ ሸጠው የሚበላ ነገር ይገዙ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ በመቀሌ ከተማ ለ15 ቀናት በቆዩባቸው ጊዜያት የከተማው ህዝብ ሰው ወዳድና አክባሪ ከመሆኑም ባሻገር ምግብና ጠላ ይገዙላቸው እንደነበር ያወሳሉ፡፡ አንዳንዶች ገንዘብም አዋጥተው ይሰጧቸው እንደነበር ገልፀዋል፡፡

መሪጌታ መኮንን ወደ ሀዋሣ ከመጡ በኋላ በ1984 ዓ.ም ወደቀድሞው ሥራቸው ተመልሰው መሥራት የጀመሩ ሲሆን ለተወሰኑ ዓመታት ከሠሩ በኋላ የመንግስት እርሻ ወደ ግል ባለሃብቶች እርሻ ይዞራል፡፡

አልሜታ ተብሎ የሚጠራው የግል ድርጅት 51 ሠራተኞችን ተረክቦ በያዙት ሥራ መደብ ያሰራቸው ነበር፡፡ መሪጌታ መኮንን ሥራ አክባሪ፣ ታታሪ፣ ትጉህ ሠራተኛ በመሆናቸው ከሠራተኞቹ ሁሉ ኮከብ ሆነው 14 ኢንች ቴሌቪዥን ተሸልመዋል፡፡

መሪጌታ መኮንን 5 ወንድ፣ 6 ሴት በድምር የ11 ልጆች አባት ናቸው፡፡ ይህ የመሪ ጌታ ምርጥ ተሞክሮ በሌሎቹም ዘንድ መለመድ እንዳለበት እየጠቆምኩኝ የዛሬን በዚሁ ቋጨሁ፡፡ ሰላም፡፡