በኮሪደር ልማት፣ የመንገድ ግንባታ እና ተያያዥ ስራዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ የጠቅላላ ተቋራጮች እና የአገልግሎት ተቋማት ትጋትና ቁርጠኝነት የሚበረታታ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 24/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀድያ ዞን ሆሳዕና ከተማ እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት፣ የመንገድ ግንባታ እና ተያያዥ ስራዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ የጠቅላላ ተቋራጮች እና የአገልግሎት ተቋማት ትጋትና ቁርጠኝነት የሚበረታታ ስለመሆኑ ተገለጸ።
በከተማው የሄጦ ቀበሌ እና ህዝቡ በመተባበር ለመሳይ ኦሊ ጠቅላላ ተቋራጭ እና የአገልግሎት ተቋማት በሀድያ ብሄር ባህል መሰረት “አሻም” ለማለት የማዕድ ግብዣ አድርገዋል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ እንደተናገሩት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረው 20ኛዉ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በከተማው የሚከበር መሆኑን ተከትሎ እንግዶችን ለመቀበል በሚያስችል መልኩ በርካታ መሰረተ ልማቶች እየተከናወኑ ይገኛል።
ከተማውን ስማርት ሲቲ ለማድረግ በተያዘው ዕቅድ መሠረት ቴክኖሎጂው የደረሰበትን ደረጃ ባማከለ መልኩ ደረጃውን የጠበቀ መሰረተ ልማት በሁሉም አቅጣጫ በፍጥነት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም ከፌዴራል እስከ ክልል የሚገኙ ባለድርሻ አካላት እያደረጉ ያለው ያልተቋረጠ ክትትልና ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ህዝቡ ካለው የልማት ጉጉት የተነሳ በገንዘብ፣ በጉልበትና በሀሳብ ተሳትፎ ከማድረግ በዘለለ በየአካባቢው የተጀመሩ የልማት ተግባራትን እያከናወኑ ያሉ ተቋማትንና ጠቅላላ ተቋራጮችን በሀድያ ባህል መሰረት “አሻም” በማለት እያበረታታ መሆኑን ገልጸው፥ በዕለቱ ለመሳይ ኦሊ ጠቅላላ ተቋራጭና ለአገልግሎት ተቋማት ሰራተኞች የሄጦ ቀበሌ ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
የከተማ አስተዳደሩ በሁሉም የልማት ተግባራት ቀን እና ማታ ሳይሉ እየተጉ ለሚገኙ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ከንቲባው አረጋግጠዋል።
የሄጦ ቀበሌ ነዋሪና የቀበሌው ምክር ቤት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ታፈሰ ቲርካሶ በበኩላቸው በከተማው የሚከናወነው የመሰረተ ልማት ተግባር በጣም የሚበረታታ በመሆኑ የሚሰራውን ሰው “አሻም” ማለት የብሄሩ ባህልም በመሆኑ የተዘጋጀ ግብዣ እንደሆነ አስረድተዋል።
በቀጣይም በሚያስፈልገው ሁሉ ህዝቡ ከጎናቸው እንደሚሆን ተናግረዋል።
አቶ ደመላሽ አባተ የሆሳዕና ከተማ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ እና የሆሳዕና-ጃጁራ-ግምቢቹ-ጃቾ መንገድ ዋና ተጠሪ አማካሪ መሃንዲስ፥ ከተማዋን በስማርት ሲቲ ስታንዳርድ ባሟላ መልኩ የዲዛይን ለውጥ በማድረግ ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸው በተቀመጠው አጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ሁሉም ሰራተኛ ቀንና ማታ ሳይል በትጋት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በስራ ላይ በነበርን ጊዜም ያየነው የህዝቡ ድጋፍና ማበረታቻ ለልማት ያላቸውን ፍላጎት የሚያሳይ እና ልማቱን የበለጠ እንድናፋጥን ከማነሳሳቱም በላይ የህዝቡ አደራ ጭምር እንደሆነ በመገንዘብ ሙሉ አቅማቸውን በመጠቀም እንደሚሰሩ አቶ ደመላሽ አረጋግጠዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ስራ አስፈጻሚ አካላት የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሄጦ ቀበሌ አስተዳደር አመራሮችና የመሳይ ኦሊ ጠቅላላ ተቋራጭ ሰራተኞች እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና የኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኞችና የቀበሌ ነዋሪዎች ታድመዋል።
ዘጋቢ: ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
በሴቶች ላይ የሚደርሱ ማህበራዊ ጫናዎችን ለመከላከል የኢኮኖሚ ባለቤት እንዲሆኑ ለማስቻል ሁሉም ባለድርሻ አካላላት ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ተገለፀ
ትምህርት ቤቶች የዉስጥ ገቢያቸዉን በማሳደግ የግብዓት ችግሮችን በመቅረፍ ምቹ የመማር ማስተማር ከባቢን መፍጠር እንዳለባቸዉ ተገለፀ
የሣውላ ከተማ ህዝብ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን አካሄደ