የጀፎረ ይዘት ተጠብቆ የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መስተጋብር ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 20/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የጀፎረ ይዘት ተጠብቆ የማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መስተጋብር በማጠናከር ለአለም ለማስተዋወቅ እየሰራ እንደሚገኝ ገለፀ።
ዩኒቨርሲቲው ውጥኑን እውን ለማድረግ ከፖላንዱ ክራኮቭ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁሟል።
የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊል ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች እና ባለሙያዎች እንዲሁም ከፖላንድ ዩኒቨርርሲቲ ኦፍ ክራኮቭ ልዑካን ጋር በቸሃ ወረዳ ጣናቃ ቀበሌ የጉራጌ ጀፎረ በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የጀፎረ ይዘት ተጠብቆ የማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መስተጋብር በማጠናከር ለአለም ለማስተዋወቅ እየሰራ ይገኛል።
“የመሬት አስተዳደር ጥቅም ለአረንጓዴ ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ በዩኒቨርስቲው በተሰናዳው ዝግጅት ከፖላንዱ ዩኒቨርርሲቲ ኦፍ ክራኮቭ እና ወልቂጤ ዩኒቨርስቲዎች ሶስት ጥናታዊ ፅሁፎች መቅረባቸውን የተናገሩት ዶ/ር ፋሪስ፥ ከተሞችን በፕላን በመምራት ለነዋሪዎቻቸው ምቹ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት ለኮሪደር ልማት የሰጠው ትኩረት ዘላቂ መፍትሄ የሚያስገኝ በመሆኑ በከተማና ገጠር ተጠናክሮ እዲቀጥል ይሰራል ብለዋል።
የፖላንዱ ዩኒቨርርሲቲ ኦፍ ክራኮቭ ልዑካን ቡድን ተወካይ ፕሮፌሰር ጆሴፍ ኸርኒክ በቸሃ ወረዳ ጠናቃ ቀበሌ ነዋሪዎች ለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነው ማህበረሰቡ በሀገር በቀል እውቀት ለዘመናት ጠብቆ ያቆየውን ውብ ጀፎረ በመንከባከብ ለአለም ማስተዋወቅ ይጠበቅበታል ብለዋል።
ሳይንሳዊና ሀገር በቀል እውቀት በማዋኸድ የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት በሚያሳድጉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ከወልቂጤ ዩንቨርሲቲ ማህበረሰብ ጋር መምከራቸው የልዑካን ቡድኑ ተወካይ ፕሮፌሰር ጆሴፍ ጠቅሰዋል።
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ስነ ፅሁፍ ትምህርት ክፍል መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ካሚል ኑረዲን ከ15ው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እዚህ የደረሰው ሀገር በቀል እውቀት ጀፎረ የማሀህበረሰቡ ፍልስፍና ጭምር አመላካች እሴት እንደሆነ አስገንዝበዋል ።
የጉራጌ ጀፎረ የዳኝነት የመመራረቂያ የሽምግልና እና የጋብቻ እንዲሁም ሌሎችም ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስነ-ስርዓቶች የሚከናወንበት ስፍራ እንደሆነ በመጥቀስ እሴቱ ቀጣይነት ያለው ጥበቃ ይፈልጋል ብለዋል ረዳት ፕ/ር ካሚል።
ጀፎረን ከጥፋት የሚታደግ ነባር ባህላዊ ሥርዓት አለን ያሉት በቸሃ ወረዳ ጠነቃ ቀበሌ አስተያየታቸውን የሰጡን የሀገር ሽማግሌዎች፥ ጀፎረ ማንም በምንም ዓይነት ምክንያት ቀድሞ የነበረውን ቅርፁን የሚለውጥ አንዳችም ዓይነት የግንባታ ሥራ እንዳያካሄድ ነባሩ የጉራጌ ብሔር ባህላዊ ሕግ ያግዳል ብለዋል፡፡
የጀፎረን ወሰን አልፎ አጥር ማጠር፣ ቤት መስራት፣ እርሻ ማረስ፣ በባህላዊው የዳኝነት ህጉ የተወገዘ ተግባር በመሆኑ እሴቱ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲሸጋገር አስችሎታል ብለዋል አስተያየታቸውን የሰጡን የሀገር ሽማግሌዎች ፡፡
ዘጋቢ፡ ሪድዋን ሰፋ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
ጤና ጣቢያው እየሰጠ ባለው አገልግሎት መደሰታቸውን ተገልጋዮች ተናገሩ
የሰላምና የመከባበር ባህልን ለማስቀጠል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ተገለፀ
የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ኑሮ ማሻሻል እንደሚገባ ተገለጸ