ከተሞችን ለኑሮ ምቹና ሳቢ ለማድረግ አመራሩ ዘርፉን በተገቢው መምራት እንዳለበት ተገለጸ

ከተሞችን ለኑሮ ምቹና ሳቢ ለማድረግ አመራሩ ዘርፉን በተገቢው መምራት እንዳለበት ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 19/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከተሞችን ለኑሮ ምቹና ሳቢ ለማድረግ አመራሩ ዘርፉን በተገቢው መምራት እንዳለበት የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳር አቶ ማቴዎስ አኒዮ ገለፁ።

የሀድያ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ አካሂዷል።

በመድረኩ የኮርደር ልማት፣ የአንድ ከተማ አንድ ፕሮጀክት ተግባራትና አጠቃላይ የሩብ ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት አፈፃፀምና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስመልከት የመነሻ ጽሑፍ ቀርቧል።

የምክክር መድረኩን የመሩት የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ እንደገለፁት ከተሞች ለኑሮ ምቹና ሳቢ እንዲሆኑ አመራሩ ዘርፉን በተገቢው መመራት አለበት ብለዋል።

በከተሞች ገቢ አሰባሰብ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች መቀረፍ አለባቸው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፥ በተለይ በማዘጋጃ ቤት ገቢ አሰባሰብ ላይ የሚታዩ ችግሮች ላይ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ የተሻለ ለማድረግ የተጀመረው የከንቲባ ችሎት ከወረቀት ባለፈ ተገቢ  አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ የህዝብን ጥያቄ ባጠረ ጊዜ ለመመለስ መስራት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።

የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለማግኘት ለተደራጁ ማህበራት፣ ለስራ አጥ ወጣቶች፣ ለኢንቨስትመንት ልማትና ለኢንዱስትሪ ዞኖች የሚቀርቡ የመሬት ዝግጅቶች ላይ ማተኮር ተገቢ እንደሆነ ተገልጿል።

እነዚህንና ሌሎች መሰል ተግባራትን ስኬታማ ማድረግ የሚቻለው ዘርፉን በተገቢው መምራት ሲቻል እንደሆነም ገልጸዋል።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ተሾመ አነሞ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ  በከተሞች ደረጃ ከታቀዱ ተግባራት መካከል በሩብ ዓመቱ በርካታ ውጤታማ ስራዎች የተከናወኑ ቢሆንም ክፍተቶች መኖራቸውን አንስተዋው ክፍተቶቹን ለመሸፈን ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል።

ከተሞችን ውብ ማራኪና ለነዋሪና ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ የተጀመረውን የኮርደር ልማት ስራ ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ የታዩ ክፍተቶችን ለመሸፈን የሚያስችል መድረክ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

በዞኑ በሰባት ከተሞች 45 ነጥብ 5 የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ስራ ለማከናወን የታቀደ ሲሆን ከዚህም 35 ኪሎ ሜትሩ በሆሳዕና ከተማ በ190 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚገነባና ከዚህም 70 ከመቶ መልማቱንም አሳውቀዋል።

ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ መሬቶችን አዘጋጅቶ ከማቅረብ ረገድ ስራዎች ቢሰሩም ከይገባኛል ነፃ አድርጎ ከማቅረብ አንጻር ውስንነቶች መታየታቸውን የገለጹት አቶ ተሾመ እነዚህን ክፍተቶች ለመሸፈን የሚያስችል ውይይት ስለመሆኑም ተናግረዋል

የከተሞችን ፕላን በማዘጋጀትና በትግበራ ላይ የሚታዩ ውስንነቶችን ለመቅረፍ በተሰራ ስራ በአጭር ጊዜ ለውጦች የተመዘገቡ ቢሆንም ቀሪ ተግባራትን ለማከናወን ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ አቶ ተሾመ ጠይቀዋል።

የሪፖርትና የመረጃ ግንኙነት ጠንካራ ያሐመሆን፣ የከተማ ገቢ አማራጮችን ለይቶና አሟጦ ያለመሰብሰብ፣ ህገወጥ የመሬት ወራራን ያለመከላከልና ህጋዊ ስርዓት ያለማስያዝ፣ የማህበራት መሬት ትልልፍ ላይ የሚታይ ኢ ፍትሃዊነት ችግር፣ለኢንዱስትሪ ዞንና ሌሎችም አግባብነት ላላቸው ጉዳዮች መሬት ማዘጋጀት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሸፈን መስራት እንደሚገባ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጓል።

ቀሪ ዕቅዶችን ከግብ ለማድረስ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አንዳለባቸውም ከድምዳሜ ተደርሷል።

ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን