የከተሞች ፎረም የልምድ ልውውጥ የሚደርግበት መድረክ ነው – ተሳታፊዎች
ሀዋሳ፣ ሕዳር 09/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የከተሞች ፎረም የልምድ ልውውጥ የሚደርግበት መድረክ ነው ሲሉ 10ኛው የከተሞች ፎረም ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡
ከ150 በላይ የክልልና የዞን ከተሞች በአፋር ክልል ሰመራ-ሎጊያ ከተማ 10ኛው የከተሞች ፎረም እየተሳተፉ ይገኛል።
ፎረሙ “የከተሞች ዕድገት ለሀገር ሁለንተናዊ ልማት” በሚል መሪ ቃል ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
በፎረሙ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል የሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ቸርነት ፍላቴ፤ 9ኛው የከተምች ፎረም በወላይታ ሶዶ በተካሄደበት ወቅት ሀዋሳ ከተማ 2ኛ ደረጃ በመውጣት ተሸላሚ መሆኗን ጠቅሰው አሁን ደግሞ ሰመራ ሎጊያ ከተማ 10ኛው የከተሞች ፎረም ለመሳተፍ ሰፊ ዝግጅት አድርገው እንደተገኙ ጠቅሰዋል።
የፎረሙ መዘጋጀት በተለያየ ዘርፍ ሀዋሳ ከተማ ለሌሎች ከተሞች ልምዷን የምታካፍልበት መድረክና ከሌሎች ከተሞች የተሰሩ ስራዎችን በማየት ልምድ የምንለዋወጥበት ነው ብለዋል።
ሌላኛው የፎረሙ ተሳታፊ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ምክትል ስራ አስኪያጅና የከተማ ፕላን ዘርፍ ኃላፊ አቶ አበሻ አሽኮ እንደተናገሩት በአስሩም የከተሞች ፎረም እንደተሳተፉ ጠቁመው ሰመራ ሎጊያ ከተማ የተዘጋጀውን ፎረም ላይ አርባምንጭን ሊገልጡ የሚችሉትን ግብአቶች ይዘው እንደቀረቡ ነው የተናገሩት።
አርባምንጭ የ2 ዓመታት የከተማዋ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች የሚያሳይ የህትመት ስራዎችን፣ አጠቃላይ ከተማውን የሚያሳይ ሞዴል፣ የፈጠራ ውጤቶች፣ የፍራፍሬ ውጤቶች፣ የአዞ እንዲሁም የአሳ ምርት እንዳመጡ ነው የገለጹልን።
ከዚህም በተጨማሪ አርባምንጭን ሊወክሉ የሚችሉ የጋሞ ሀገር ሽማግሌዎችን በማምጣት ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶችን በጠበቀ መልኩ ሌሎች ክልሎች የዱቡሻ ስርአትን የጋሞ ባህላዊ እሴትን የምናሳይበት ነው ብለዋል።
የከተሞች ፎረም የእኛን ልምድ ብቻ የምናጋራበት ሳይሆን ከሌሎችም የልምድ ልውውጥ የምናደርግበት ነው ብለዋል።
አቶ ትዕግስቱ ጂባ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የፎረሙ ተወካይ እንደተናገሩት፤ ከተማዋ ቀደም ሲል የነበረችበትና አሁን የደረሰችበትን ሞዴል፣ በቱሪዝም ዘርፍ የጉራጌ ባህል ምግብ፣ ባህላዊ ቁሳቁሶች፣ ይዘው እንደቀረቡ ጠቁመዋል፡፡
10ኛው የከተሞች ፎረም በሰፊው ዝግጅት የተደረገበት እንዲሁም አንዱ ከተማ ከሌላ ከተማ ልምድ የተለዋወጡበትና ስጦታም በመለዋወጥ ፍቅራቸውን የተገላለጹበትም ስለመሆኑ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
ዘጋቢ: ሐና በቀለ

More Stories
የዞኑ ሕዝብ ከማርበርግ ቫይረስ ራሱን መጠበቅ እንዲችል የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ አሳሰበ
በልማትና በመልካም አስተዳደር የሚነሱ ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ
የባስኬቶ ዞን ላስካ ዙሪያ ወረዳ ህዝብ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 10ኛ የሥራ ዘመን 1ኛ አስቼኳይ ጉባኤ አካሄደ