ጠንቀኛው በሽታ
በፈረኦን ደበበ
በሽታ ከምንበላቸው፣ ከምንጠጣቸውና ከህይወት ዜይቤ እንደሚነሳ ግንዛቤ ያደገው አሁን ነው፡፡ የአብዛኞች እምነት ከመቅሰፍት ጋር እንደሚያያዝ ነበር፡፡ የዚህ በሽታ ባህሪ ግን ከዚህ ሁሉ ይለያል፡፡
እንደ ሌሎች በዓይን በማይታዩ ተህዋሲያን አማካይነት ሳይሆን ተጨባጭና በምንበላቸው ምግቦች አማካይነት መሆኑ አደገኛ ያደርገዋል፡፡ ሰው ምግብ የሚበላው ጤነኛና ደስተኛ ለመሆን እንጂ ተመልሶ ህይወቱን የሚያጣ ከሆነ እንዴት ማቃናት ይቻላል?
አልፎ ተርፎ የህብረተሰቡ የዕድገት ደረጃና የኑሮ መሻሻል መጨመሩም ሰው ራሱን እንዲጠላ የሚያደርግ ነው፡፡ ያደጉ ሀገራትና የባለጸጎች የሚባለው ይኸው በሽታ፣ በአሁኑ ወቅት ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች እየጎዳ ሲሆን የህክምና ባለሙያዎችም ህብረተሰቡ የአመጋገብ ሥርዓቱን እንዲያስተካክል ምክረ-ሀሳባቸውን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
በተፈጥሮ ከሚነሳው በተጨማሪ ከሰውነት ውፍረት ጋር እንደተያያዘ የሚነገርለት ሲሆን በታዳጊ ሀገራት ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩም በመገናኛ ብዙሀን ተወስቷል፤ ካላቸው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ አንጻር በቂ ህክምና ማግኘት ስለማይችሉ፡፡
በእንግሊዝኛ “ዲያቤትስ” ተብሎ የሚጠራው ይህ በሽታ፣ “ዓይነት-1” እና “ዓይነት-2” የተሰኙ ሁለት ደረጃዎች ሲኖሩት በሰውነታችን ውስጥ እየተካሄደ ያለው የምግብ መንሸራሸር እንዲዛባ ማድረጉንም “ፌይር ኦብዘርቨር” የተባለው ድረ-ገጽ አስታውቋል፡፡
በደማችን ውስጥ ያለው ግሉኮስ የተባለው ንጥረ-ነገር ወይም ስኳር ከመጠን በላይ ከማደጉ እንደሚነሳ የሚነገርለት ህመሙ የኋላ ኋላ በልብ፣ የደም ቧንቧ፣ ኩላሊት እና ነርቮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስም ነው የተነገረው፡፡
ሰውነት “ኢንሱሊን” የተባለውን ንጥረ-ነገር በበቂ መጠን ካለማመንጨት ይከሰታሉ የተባሉት እነዚህ የስኳር ህመም ዓይነቶች አንዱ ከሌላው እንዴት እንደሚለያይም ድረ-ገጹ የጠቀሰው መጠንን መሠረት በማድረግ ነው፡፡
ዓይነት-1 የወጣትነት በሽታ ወይም “በኢንሱሊን” ላይ ተቀጽላ የሆነ የስኳር ህመም መባሉን ጠቅሶ መነሻውም ጣፊያ ኢንሱሊን የተባለውን ንጥረ-ነገር ማምረቱን ሲያቆም መሆኑን አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል ዓይነት-2 ብዙውን ጊዜ ዕድሜያቸው ከፍ ባሉ ሰዎች ላይ ሲከሰት መንስኤውም ሰውነታቸው ኢንሱሊንን በመዋጋት በበቂ ሁኔታ ማምረት አለመቻል መሆኑን ጠቅሶ ከሁለቱ ህመም ዓይነቶች ጋር የሚኖር ሰው በቂ ህክምናም ሆነ ኢንሱሊን ማግኘት እንዳለበት አስታውቋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ 830 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ስኳር ህመምተኛ እንደሆኑ ገልፀው “ፌይር ኦብዘርቨር”፣ ከእነዚህ መካከል ብዙዎች በቂ ህክምና ያለማግኘታቸውንም ነው ያስታወቀው፡፡ የህክምና ዋጋ መወደድም በተለይ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሰዎች ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ነው በተለይ የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ መግለጫ ያወጣው፡፡ የድርጅቱ ዳይሬክተር ጀኔራል ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም በዚህ ጊዜ እንደተናገሩት ከሆነ ሥርጭቱ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን ይህም ከውፍረት መጨመር፣ ጎጂ ሊሆኑ የሚችሉ ምግቦችን ገዝቶ በመመገብ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባለማድረግ እና በኑሮ ጫና እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አፍሪካን ጨምሮ በርካታ ተጎጂዎች ባሉበት ሁኔታ ስለ መከላከያ ዘዴው ሲያወሱም ሀገራት ጤናማ የአመጋገብ ዘይቤ እንዲኖራቸው ፖሊሲ ማውጣት እንደሚያስፈልግ ተናግረው ከዚህ ሁሉ በላይ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ ምርመራ፣ መከላከልና በህክምና ላይ ያተኮረ ጤና ፖሊሲ ማስፈለጉንም ነው ያስታወቁት፡፡
አፍሪካ ኒውስ የተባለው ዜና ማሠራጫ ያወጣው ዘገባም ከዚህ ጋር የተጣጣመ ነው፤ በተለይ በቅርቡ ከሠሀራ በታች የሚገኙ ሀገራትን በማስመልከት ባወጣው ዘገባ የሚሰጠው ህክምና በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ በመግለጽ፡፡
የበሽታው ዋነኛው ጫና በደቡብ አፍሪካ እንደሆነ በሚነገርበት በአሁኑ ጊዜ በየዓመቱ 17 ሚሊዮን የሚሆኑና ዕድሜያቸው 70 ያልደረሱ ሰዎች መሞታቸውንም ነው ያስታወቀው፡፡ ከሠሀራ በታች ከ5 እስከ 10 በመቶ ብቻ ህክምና ከማግኘታቸው ጋርም አያይዘው ነው ዶ/ር ቴዎድሮስ የተናገሩት አፋጣኝ መፍትሄ ማስፈለጉን በማስታወቅ፡፡
የበሽታው ሥርጭት በጣም አሳሳቢ እንደሆነ ያስታወቁት ዶ/ር ቴዎድሮስ በመከላከል፣ በቅድመ ምርመራና ህክምና ላይ ትኩረት የሚያደርግ ፖሊሲ ማስፈለጉንም ነው ያስታወቁት፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2030 የበሽታውን ክብካቤ አሁን ካለበት ከፍ ለማድረግ የያዘው ዕቅድ በአህጉሪቱ ምርመራ ለማሳደግና ጤናና ተስፋ ለማለምለም እንደሚረዳም ነው የተነገረው፡፡
ዘ ኮንቨርሴሽን የተባለው ድረ-ገጽ ስለ አህጉሪቱ ባወጣው ዘገባም ከ9 ደቡብ አፍሪካዊያን አንዱ በህመሙ እንደሚሰቃይ ጠቅሶ በአሁኑ ጊዜ ወደ 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከበሽታው ጋር መኖራቸውንም ነው ያስታወቀው በተለይ በሴቶች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በመጠቆም፡፡
በዓለም ላይ ስምንተኛው የሞትና የአካል ጉዳት መንስኤ እንደሆነ የሚነገርለት የስኳር በሽታ አግባብ የሆነ ህክምና ካልተደረገለት ለነርቭ ጉዳት፣ ለኩላሊትና ልብ ህመም፣ ምች፣ ለእይታ መሠወርና እንዲሁም ለአዕምሮ መዛባት መዳረጉም ነው የተነገረው፡፡
ሰፊ መዘዝ ያለበት ይህ በሽታ በሀገራችን ኢትዮጵያም ብዙ ሰዎቻችን በማሰቃየት ላይ ሲሆን በተለይ የሚፈልገው ከፍተኛ የህክምና ወጪም ለብዙዎች ጉልበት አሳጥቶ ለጉስቁልናና ለሞት ዳርጓቸዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ህዝቡም የአመጋገብ ሥርዓቱን ቀይሮ ለበሽታው የሚያጋልጡ ምግቦችን መቀነስ ይኖርበታል፡፡
More Stories
“ጉንፋን በአንቲባዮቲክስ መድሀኒቶች አይታከምም” – ዶክተር ሚስጥር አወቀ
እርቅ
የአምራች ዘርፉን የመቀላቀል ውጥን