የዞኑ ሕዝብ ከማርበርግ ቫይረስ ራሱን መጠበቅ እንዲችል የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ አሳሰበ

የዞኑ ሕዝብ ከማርበርግ ቫይረስ ራሱን መጠበቅ እንዲችል የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ አሳሰበ

የአደጋ ጊዜ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ግብረ ሀይል ተዋቅሮ በሽታው እንዳይከሰት አስቀድሞ የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ።

በክልሉ በኣሪ ዞን በጂንካ ሆስፒታል የበሽታው መከሰት ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ በጋሞ ዞን የበሽታው ስርጭት እንዳይስፋፋ በሁሉም የጤና ማዕከላት ግብረ ሀይል ተዋቅሮ የግንዛቤ እና አስቀድሞ የመከላከል ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ ሰይፉ ዎናቃ ተናግረዋል።

ዞኑ በሽታው ከተከሰተበት ኣሪ ዞን ጋር በተለያዩ ማህበራዊ እና ሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩ የተጠናከረ በመሆኑ የበሽታውን መንስኤ እና መከላከያ ዘዴዎችን በተመለከተ ለሕብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ እየተሰጠ መሆኑን የገለጹት አቶ ሰይፉ ቫይረሱ በንኪኪ እና ከአፍ እና አፍንጫ እንዲሁም ከሰውነት በሚወጡ ፈሳሾች አማካኝነት የሚተላለፍ በመሆኑ በእንቅስቃሴ ወቅት ህብረተሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ መክረዋል።

በዞኑ ባሉ በሁሉም የጤና ተቋማት ግብረ ሀይል ተዋቅሮ እየተከታተለ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሰይፉ በዞኑ በሁለት አጠቃላይ ሆስፒታሎች የልየታ ማዕከላት መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

የአደጋ ጊዜ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ማእከላትና የህክምና ተቋማትን በማጠናከር የመከላከሉ ሥራ ተጠናክሮ እየተሰራ መሆኑን አቶ ሰይፉ አብራርተዋል።

በዞኑ እስከ አሁን በበሽታው የተያዘ ሰው አለመኖሩን የመምሪያው ሀላፊ አክለዋል።

ዘጋቢ: ወ/ገብርኤል ላቀው – ከአርባምንጭ ጣቢያችን