በተፈጥሮ እግራቸዉ ቆልማማ ወይም ተጣሞ ለሚወለዱ ህፃናት ህክምና መስጠት የሚያስችል የግንዛቤ መፍጠሪያ ስልጠና ተሰጠ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 19/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኦሞ ዞን በማሌ ወረዳ በተፈጥሮ እግራቸዉ ቆልማማ ወይም ተጣሞ ለሚወለዱ ህፃናት ህክምና መስጠት የሚያስችል የግንዛቤ መፍጠሪያ ስልጠና ለጤና ባለሙያዎች ተሰጥቷል።
የግንዛቤ መፍጠሪያ ስልጠናዉ የተሰጠው ሆፕ ወክስ በተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት አማካኝነት ሲሆን በደቡብ ኦሞ ዞን ስር ከሚገኙ የመንግስት ጤና ተቋማት መካከል ለኮይቤ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እና ለበነታ ጤና ጣቢያ ባለሙያዎች ነዉ።
ስልጠናዉን የሰጡት በሆፕ ወክስ ድርጅት የፕሮግራም አስተባባሪና የጤና ባለሙያ አቶ ዳግም ታምሬ እንደተናሩት፤ በእንግሊዘኛው አጠራር “ከልብ ፉት” ወይም ቆልማማ እግር የተሰኘዉ የህፃናት አንዱ ወይም ሁለቱ እግሮች በተፈጥሮ ወደ ዉስጥ ቆልማማ ሆኖ መወለድ ችግር ነው፡፡
በዚህም ችግር የሚወለዱ ህፃናት በወቅቱ ህክምና ካገኙ ሙሉ በሙሉ ሊድን የሚችል መሆኑን ገልፀው ከጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ጋር በመተባበር ድርጅቱ የነፃ ህክምና አገልግሎት አየሰጠ አንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በደርጅቱ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ ወ/ት ኤልሳቤጥ በላይ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ወደ ስልሳ ሶስት በሚሆኑ የመንግስት ጤና ተቋማት አገልግሎቱን በመስጠት ከ20ሺህ ህፃናት በላይ በማከም ማዳን መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጂንካ ሆስፒታልን ጨምሮ በሶዶ፣ በኦቶና ሆስፒታል፣ በዲላ እና አርባምንጭ ሆስፒታሎች የነፃ ህክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
በስልጠናው ተሳታፊ ከነበሩ የጤና ባለሙያዎች መካከል ሲስተር ተስፋነሽ ተምቤል እና አቶ ባንዳ ባደገ በጋራ በሰጡት አሰተያየት፤ በችግሩ ተጠቅተዉ የሚወለዱ ህፃናት ወደ ህክምና ቦታዉ ሄደው ታክመዉ እንዲድኑ በማድረግ ረገድ የበኩላቸውን ሀላፊነት እንደሚወጡ አስረድተዋል።
የኮይቤ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ወንዱ ቤራ በበኩላቸው፤ የሆፕ ወክስ ግብረ ሰናይ ድርጅት እየሰጠ ለሚገኘው የህክምና አገልግሎት እና ለጤና ባለሙያዎች የተሰጠው የግንዛቤ ፈጠራ ስልጠና አመስግነዋል፡፡
የማሌ ወረዳና አጎራባች አከባቢዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የበለጠ ስለ ችግሩ ግንዛቤ ኖሯቸዉ እንዲታከሙ እንደሚያደርጉ አመላክተዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ዳኛቸው ደሴ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው
የምስራቅ ጉራጌ ዞን አስተዳደር ከዞኑ ከተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በቡታጅራ ከተማ ወይይት በማካሄድ ላይ ይገኛል
ከአገልግሎት አሰጣጥ አንፃር ከዞን እስከ ወረዳ የህዝቡን አስተያየት መሠረት በማድረግ በተሰራው ስራ የመልካም አስተዳደር ችግሮች የተፈቱበት በጀት አመት ነበር ሲል የቤንች ሸኮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ገለፀ