የተለያዩ አልባሳትን በማምረት ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ እንደሚገኙ በሽመና ሥራ ማህበር የተደራጁ አባላት ገለጹ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 19/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በወላይታ ዞን በኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ በሀላሌ ከተማ በማህበር ተደራጅተዉ በሥራ ላይ የሚገኙ “ዲዳዬ ድቻ” የሽመና ሥራ ማህበር በሥራዉ የወላይታ ብሔር ባህልን የሚገልጹ የተለያዩ አልባሳትን በማምረት ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ መሆኑን የማህበሩ አባላት ተናገሩ።

በወረዳዉ የሀላሌ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት በበኩሉ፥ በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች አስፈላጊዉን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል።

“ዲዳዬ ድቻ” የሽመና ሥራ ማህበር እንደ ማህበር የተደራጀው በ2015 ዓ.ም ሲሆን ማህበሩ ከተመሰረተ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከአካባቢዉ አልፈዉ ለሌሎች አጎራባች ወረዳዎችም ጭምር በበቂ ሁኔታ ምርታቸዉን በማቅረብ በርካታ ደንበኞችን ማፍራታቸዉን የማህበሩ አባላት መካከል ወጣት ታምራት ገርማሞ እና ኪዳኔ ኪንፌ ተናግረዋል።

የተለያዩ የብሄር ብሄርሰቦችን ባህላዊ አልባሳትን በልዩ ልዩ ቀለምና ዲዛይን በማምረት ለገበያ የሚያቀርቡት “የዲዳዬ ድቻ” የሽመና ሥራ ማህበር፣ በ75ሺህ ብር መነሻ ካፒታል ሥራዉን የጀመረ ሲሆን እስካሁን ይበል የሚያሰኝ ጥሪት መሰብሰቡን ወጣቶቹ ገልጸዋል።

ጥሬ እቃዎችን ከገበያ በመግዛት ባህላዊ አልባሳትን አምርተዉ ለገበያ እንደሚያቀርቡ እና የማምረቻና የመሸጫ ቦታ ጥብበት መኖሩ ደግሞ በኢኮኖሚያዊ እድገታቸዉ ላይ ስጋት እንደጫረም ተናግረዋል።

በኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ የሀላሌ 01 ቀበሌ አንድ ማዕከል አስተባባሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ኮላሶ በበኩላቸዉ፥ እንደ ቀበሌያቸዉ ለተለያዩ ወጣቶች የሥራ እድል እንደተመቻቼ አንስተዉ ከእነዚህም መካከል “ዲዳዬ ድቻ” የሽመና ሥራ ማህበር ለሌሎች ተምሳሌትነትን ያተረፈ ውጤታማ ማህበር ስለመሆኑ ገልፃዋል።

በኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ ኢንተርፕራይዞች እና ኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መሰረቱ ዳላቾ፤ በወረዳዉ ዉስጥ ላሉ ወጣቶች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ እድል ለመፍጠር በታቀደው ዕቅድ መሰረት  በርካታ ወጣቶች ወደ ሥራ የገቡ ስለመሆናቸው አንስተዉ፣ በቀጣይ ከዚህ በላቀ ሁኔታ ሌሎችንም ወደ ሥራ የማስገባት ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ  አስረድተዋል።

እንደ ምክትል ኃላፊዉ ገለፃ፥ ባለፉት ጊዜያት ከኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ሀላሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር ለተለያዩ ማህበራት የገንዘብ ብድር ማመቻቸት ተችሏል።

እንዲሁም ሌሎች ማህበራትም ከአበዳሪ ተቋማት  የገንዘብ ብድር  አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ዘርፈ ብዙ ጥረቶች መከናዎናቸውንና በተቀመጠ የጊዜ ገደብ መሰረት ብድር የማስመለስ ሥራም እየተከናወነ ይገኛል።

የሀላሌ ከተማ ማዘጋጃ ጽ/ቤት ዋና ኃላፊ አቶ ማርቆስ ማቴዎስ በበኩላቸዉ፥ “በከተማዉ በማህበር ለሚደራጁ ወጣቶች የንግድ ቦታ ከማመቻቸት አኳያ ከወትሮው በተሻለ ሁኔታ ላይ የሚንገኝ ቢሆንም አሁንም የማህበራትን ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ ሼዶችን እና ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የድጋፍና ክትትል ሥራዎችን  እየሰራን እንገኛለን” ብለዋል።

ኃላፊዉ አክለዉም፤ ከዚህ በፊት የተለያዩ የንግድ ሱቆችን እና የመሳሰሉትን ገንብተዉ ለማህበራት ያሰራጩ መሆኑን በመጠቆም፤ በቀጣይ ሰፋ ያሉ የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎችን ለመገንባት መታቀዱንም አመላክተዋል።

ዘጋቢ: ማቱሳላ እርዳቸዉ – ከዋካ ጣቢያችን