በገጠር ተደራሽ መንገድ ፕሮግራም ለሚሰሩ ስራዎች ከ134 ሚሊየን ብር በላይ በጀት በመመደብ እየሠራ እንደሚገኝ የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ አስታወቀ

በዘንድሮው በጀት አመት በገጠር ተደራሽ መንገድ ፕሮግራም ለሚሰሩ ስራዎች ከ134 ሚሊየን ብር በላይ በጀት በመመደብ እየሠራ እንደሚገኝ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ አስታውቋል።

ቢሮው ሁሉን አቀፍ የገጠር ቀበሌዎች ተደራሽ መንገድ የ2017 ዓ.ም የፕሮጀክቶች ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በቀቤና ልዩ ወረዳ ጣጤሳ ወሸርቤ ቦቶ ድልድይ ግንባታ ፕሮጀክት ተጀምሯል።

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ተወካይና የጽ/ቤቱ ሃላፊ አቶ አማን ኑረዲን በመርሃ-ግብሩ ላይ እንደገለፁት፤ የመንገድ መሠረተ ልማት ለአንድ ሃገር እድገት ቁልፍ ሚና አለው።

የክልሉ መንግስት ይህንን ታሣቢ በማድረግ ልዩ ትኩረት በመሥጠት በዘንድሮ በጀት አመት በገጠር ተደራሽ መንገድ ፕሮግራም ለሚሰሩ ስራዎች ከ134 ሚሊየን ብር በላይ በጀት በመመደብ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሀላፊው አክለውም የተመደበው በጀት በክልሉ የበጀት ቀመር መሠረት በሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በሚሠሩ የመንገድ ልማት ስራዎች እንዲውል እንደተደረገ ገልፀው የ2017 ዓ.ም የክልሉ የገጠር ተደራሽ መንገድ ስራ በይፋ መጀመሩንም ተናግረዋል።

በቀቤና ልዩ ወረዳ የጣጤሳ ወሸርቤ ቀበሌ የቦቶ ወንዝ የድልድይ ግንባታ 12 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን ለግንባታው 10 ሚሊየን 679 ሺህ 231 ብር ወጪም በክልሉ ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት ቢሮ እንደሚሸፈንም አቶ አማን ገልፀዋል።

የልማት ሥራ በመንግሥት በጀት ብቻ ተደራሽ እንደማይደረግ የገለፁት ሃላፊው የመንገድ ስራ ከፍተኛ ሃብት የሚጠይቅና የህብረተሰቡን ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ለዚህም የክልሉ መንግስት በህብረተሰቡ ተሣትፎ ለሚገነቡ መንገድ ስራዎች ከ8 መቶ ሚሊየን ብር በላይ እቅድ መያዙን ገልጸዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ በበኩላቸው፤ መንገድ የማህበራዊ ግንኙነትን ከማጠናከር ባሻገር ያለ መንገድ ልማት የኢንቨስትመንት እና ምርትን ወደ ገበያ ማድረስ እንዲሁም ቀልጣፋ አገልግሎት መሥጠት አዳገች መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ሞሳ አክለውም የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የጣጤሳ ወሸርቤ ቦቶ ድልድይ ግንባታ ሒደት በተጠየቀ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ በመስጠታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በልዩ ወረዳው መሠረተ ልማት ችግር መኖሩን ጠቅሰው የክልሉ መንግስት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

በድልድይ ግንባታ ማሥጀመሪያ መርሃግብር ላይ አግኝተን ያነጋገርናቸው የቀበሌው ነዎሪዎች በሰጡት አስተያየት፤ የቦቶ ወንዝ ሲሞላ እናቶችና ህፃናትን በመውሰድ ከፍተኛ አደጋ ያደርስ እንደነበር ገልጸው የድልድይ ግንባታ መጀመሩ የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር የሚያቃልል በመሆኑ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ፍስሃ ክፍሌ – ከወልቂጤ ጣቢያችን