በክልሉ የሚገኙ ህብረ ብሔራዊ ልዩነቶችንና ፀጋዎችን በአግባቡ በመጠቀም የተሻለ ተግባቦትና አንድነት መፍጠር እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብሄረሰቦች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ገመቹ አረቦ ገለፁ

19ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወልቂጤ ክላስተር አመራሮችና ሰራተኞች በፖናል ውይይትና በልዩ ልዩ ሁነቶች በድምቀት አክብረዋል፡፡

በዓሉ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የብሄረሰቦች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ገመቹ አረቦ፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ባለፉት አመታት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት ሲከበር መቆየቱን አውስተዋል፡፡

ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአርባምንጭ ከተማ እንደሚከበር ገልፀው የበዓሉ መከበር የማህበረሰቡን አንድነት እንዲሁም ህገመንግሰታዊ ስርዓቱን ለማጠናከር ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ ህብረ ብሔራዊ ልዩነቶችንና ፀጋዎችን በአግባቡ በመጠቀም የተሻለ ተግባቦትና አንድነት መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡

በተለይም በጠረጴዛ ዙሪያ የመወያየትና የመነጋገር ባህልን በማሳደግ በክልሉ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን ማጠናከር እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡

የጋራ ትርክትና ህብረ ብሔራዊ እንድነት ለማጽናት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ያሉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊና የመሠረተ ልማት ክላስተር ማስተባባሪያ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አማን ኑረዲን ናቸው፡፡

በክልሉ በሚገኙ ተቋማት አካታችና አሳታፊ የሆነ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በበዓሉ ላይ በኢትዮጵያ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም ስርዓት ግንባታ ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ ሀሳብ ላይ ትኩረት ያደረገ የመወያያ ሰነድ የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ አማካሪ አቶ ያሲን ሳኒ አቅርበዋል፡፡

በመድረኩ ላይ በቀረበው ሰነድ መነሻነትም ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

በተለይም የበዓሉ መከበር ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች ለሌላው ከማስተዋወቅ ባሻገር ሀገራዊ አንድነት ለማጎልበት ጉልህ ድርሻ እንዳለው የበዓሉ

ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡

በዓሉን “ሀገራዊ መግባባት፤ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጨምሮ 9 በወልቂጤ ክላስተር የሚገኙ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች በጋራ በፖናል ውይይትና በልዩ ልዩ ሁነቶች በድምቀት አክብረዋል።

ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን