በተግባር የተደገፈ ትምህርት የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበርክት ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 18/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተግባር የተደገፈ ትምህርት የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበርክት በዳውሮ ዞን ማረቃ ወረዳ የጎዞ ባሙሽ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ገለፁ፡፡
ትምህርት ቤቱ በበኩሉ በተግባር የተደገፈ ትምህርት ለተማሪዎች የደረጀ እውቀትን ለማስጨበጥ ከማስቻሉም በላይ ለትምህርት ቤቱ አማራጭ የገቢ ማስገኛ አቅም ጭምር ስለመሆኑ አስታውቋል፡፡
ትምህርት ቤቶች ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን ለተማሪዎቻቸው ተጨማሪ የተግባር እውቀት እንዲሁም ለትምህርት ቤቱ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝላቸውን ተግባር እያከናወኑ ይገኛሉ።
ተማሪ ምናሴ መድኅን እና ተማሪ ሰለሞን ባፌ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ሲሆኑ በትምህርት ቤታቸው በተግባር የተደገፈ ትምህርት መኖሩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ያልነበረው የእርሻ ትምህርት አሁን ላይ መማር በመጀመራቸው ክፍል ውስጥ የሚሰጠው ንድፈ ሃሳብ በተግባር ማሣ ላይ ማየታቸው የተሻለ ግንዛቤ እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ቤተሰቦቻችን ከባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ እንዲላቀቁ ከእርሻ ትምህርት በቀሰምነው እውቀት መሠረት እንዲተገብሩ እያደረግን እንገኛለን ብለዋል።
በትምህርት ቤቱ የእርሻ መምህር የሆኑት መምህር አወቀ አበራ እንደገለጹት፤ ከንድፈ ሀሳብ በተጨማሪ በማሣ ላይ እንዲገኙ በማድረግ ስለ አስተራረስ፣ አዘራር፣ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ አረም ቁጥጥርና ስለምርት አሰባሰብ የሚገለጹ የግብርና ሳይንስ እውቀት የማስጨበጥ ሥራ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።
የእርሻ ትምህርት በተግባር አስደግፎ ማስተማር ለተማሪው ነገ ሌላ የሥራ አማራጭ ሊሆን እንደሚችልም ተናግረዋል።
የጎዞ ባሙሽ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ደምሴ ኡሸቾ በበኩላቸው፤ በትምህርት ቤታቸው የሚገኘውን ሦስት ሄክታር ለእርሻ የሚሆን ማሣ መኖሩን ተከትሎ ተማሪዎቻቸውንና የአካባቢው አርሶ አደሮች አዳዲስ የእርሻ ሥራዎችን እንዲቀስሙ እንደ ሠርቶ ማሳይም እየተጠቀሙ እንደሆነ አስረድተዋል።
ከዚሁ ማሣ የለሙት ሰብሎችም ሆነ የጓሮ አትክልቶች ተሸጠው የውስጥ ገቢ በመሆን ለመማር ማስተማር ሥራ አጋዥ የሆኑ ግብአቶችን ለማሟላት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለዚሁ ተግባርም የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ዘር በመስጠት፣ ግብአት በማሟላት፣ ፀረ አረምና ፀረ በሽታ የሚያጠፋ መድኃኒት በማቅረብ እንዲሁም ለተማሪዎች ተጨማሪ እወቀት እንዲያገኙ ሙያተኞችን በመመደብ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የማረቃ ወረዳ ግብርና፣ ደን፣ አካባቢ ጥበዋናና ኀብረት ሥራ ጽህፈት ቤት የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ እና ምክትል ሃላፊ አቶ ሙሉቀን ጦፉ፤ በየትምህርት ቤቶች በእርሻ ትምህርት ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ እውቀት እንዲያገኙ እና ትምህርት ቤቱ በእርሻ ሥራ ኢኮኖሚውን እንዲያጎለብት ትልቅ ሚና መኖሩን ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቶች ባላቸው ማሣ ስነ-ምህዳሩን ተከትለው እንዲያለሙ ምርጥ ዘርን ጨምሮ ሙሉ የግብርና ቴክኖሎጂ ግብአት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ አሸናፊ ግዛዉ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
19ኛው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሄራዊ አንድነት በሚል መሪ ሀሳብ በማረቆ ልዩ ወረዳ በድምቀት ተከበረ
19ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሲያከብሩ አንድነታቸውን በማጠናከር እና ሰላማቸውን በማስጠበቅ እንደሆነ የምእራብ ኦሞ ዞን የበአሉ ተሳታፊዎች ገለጹ
ከደረሰኝ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት የነጋዴው ማህበረሰብ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ ተጠቆመ