ከደረሰኝ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት የነጋዴው ማህበረሰብ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 18/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክልሉ ከደረሰኝ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት የነጋዴው ማህበረሰብ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ ጥሪ አቅርቧል።

ቢሮው ከካፋ ዞን ገቢዎች መምሪያ ጋር በመተባበር በአዲሱ የደረሰኝ ህትመትና ፍቃድ አሰጣጥ ዙሪያ ለደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች የክህሎት ስልጠና ሰጥቷል።

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊና የገቢ ጥናት፣ የታክስ፣ ትምህርትና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፀደቀ ከፍታው እንዳሉት፤ በክልሉ ከገቢ አሰባሰብ ስርዐቱን ዘመናዊ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነዉ።

በተለይም ከደረሰኝ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ያልተገባ የግብር መሰወር እየተበራከተ በመሆኑ ይህንን ችግር ለመፍታት ተከታታይነት ያለዉን የግንዛቤ ማስጨበጫ የመስጠት ስራ እየተከናወነ ነዉ ብለዋል።

የካፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ንጉሴ በበኩላቸው፥ ገቢ ለአንድ አካባቢ ሁለንተናዊ ለዉጥ ያለዉን ፋይዳ በመገንዘብ በየደረጃው የሚገኙ አካላት የገቢ ስራ ላይ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የአካባቢውን የገቢ አቅም ለማሳደግ የነጋዴው ማህበረሰብ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፤ በዘርፉ የሚስተዋለውን የደረሰኝ አጠቃቀም ችግር መፍታት እንደሚገባም አሳስበዋል።

በደረሰኝ ግብይት እንዲፈጽሙ ኃላፊነት ከተሰጣቸው በኋላ አንዳንድ ነጋዴዎች ህጋዊ ግብይት ለመፈጸም ዝግጁ አለመሆናቸውን አንስተው፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከሚፈጠረው ቅጣት የነጋዴው ማህበረሰብ ህጋዊ ግብይት በመፈጸም ራሱን መጠበቅ ይገባዋል ብለዋል።

የቦንጋ ከተማ ገቢዎች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍሬዉ አበበ በበኩላቸው፤ ከደረሰኝ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ በከተማ አልፎ አልፎ ችግሮች እንደሚስተዋሉና በተያዘው ዓመት ያለደረሰኝ ሲገበያዩ የተያዙ 10 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል ብልዋል።

የዛሬው ስልጠናም ነጋዴዎች ከደረሰኝ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ያለባቸውን የግንዛቤ ችግር የሚፈታ እንደሆነም አመላክተዋል።

የስልጠናው ተሳታፊ ነጋዴዎች በሰጡት አስተያየት፤ በደረሰኝ ግብይት መፈጸም ለመንግሥት ገቢ ከማስገባት ባለፈ ህሳብን በአግባቡ ለመምራት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለዉ ገልጸዋል።

አሁን በአዲሱ የደረሰኝ አጠቃቀም ዙሪያ የተሰጣቸው ስልጠናም ባለማወቅ ይገቡበት ከነበረው ቅጣት የሚጠብቃቸው እንደሆነም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ አሰግድ ሣህሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን